የመንግስትና የህዝብ ውስን ሃብት ለታለመለት አላማ ብቻ እንዲውል ለማስቻል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለፀ
ሀዋሳ፡ ጥቅምት 12/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የጉራጌ ዞን ምክር ቤት የመንግስትና የህዝብ ውስን ሃብት ለታለመለት አላማ እንዲውል ለማስቻል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የዞኑ ምክር ቤት የ2018 በጀት አመት የኦዲት ግኝት አስመላሽ ግብረ-ሀይል የንቅናቄ መድረክ በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።
የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ኸይሩ መሀመድ የዞኑ የኦዲት ግኝት አስመላሽ ግብረ-ሃይል አባላት የንቅናቄ መድረክ በንግግር በከፈቱበት ወቅት እንዳሉት በዞኑ ያለው የኦዲት ግኝት አስመላሽ ግብረ-ሃይል ዋና ተግባር በሁሉም መዋቅሮች የመንግስትና የህዝብ ውስን ሃብት ሳይባክን ለታለመለት አላማ እንዲውል ማስቻል ነው።
እንደ ዋና አፈ ጉባኤው ገለጻ፥ የኦዲት ግኝቶች ትርጉም የሚኖራቸውና የተፈለገው ለውጥ የሚያመጡት ከግኝቱ በመነሳት ተጨባጭ እርምጃ ሲወሰድና የተሰጡ አስተያየቶችም በዓግባቡ ሲተገበሩ ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ባለፉት አመታት የተመዘገቡ መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋት እንዲሁም ክፍተት የታየባቸው መዋቅሮች በፍጥነት በማረም በቀጣይ የተሻለ ስራ መስራትና በግለሰቦች ዘንድ የሚገኙ የመንግስት ሃብቶች ሰብስቦ ወደ ልማት ለማስገባት የክትትልና ቁጥጥር ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።
በዞኑ በኦዲት ግኝት መረጃ አያያዝ ላይ አበረታች ስራዎች መስራታቸውን የገለጹት የጉራጌ ዞን ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ አብዱ ሀሰን በግኝት አመላለስ ላይ የመዋቅሮችን ውጤቶች ለማቀራረብ ቅንጅታዊ አሰራሮች አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አመላክተዋል።
ግብረ ሀይሉ ቅንጅታዊ አሰራሮችን በመከተልም በኦዲት ግኝት ላይ የእርምትና የማስተካከያ እርምጃ በመውሰድ ያልተመለሱ የህዝብ ሀብቶችን እንዲመለሱ ማድረግ እንዳለበት ጠቁመዋል አቶ አብዱ ።
ከዞኑ የተሻለ አፈፃፀም ካስመዘገቡ መዋቅሮች መካከል የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር እና የጉመር ወረዳ ዋና አፈ ጉባኤዎች በሰጡት አስተያየት የህዝብ ሀብት ከብክነት ለመከላከል መድረኩ ልምድ የተወሰደበት መሆኑን በመጥቀስ ከኦዲት ግኝቶች በመነሳት የመንግስትና የህዝብ ሀብት ለታለመለት አላማ በማዋል የህዝብ ተጠቃሚነት እንዲጎለብት በቅንጅት መስራት ይገባል ብለዋል።
ባለፉት አመታት የተመዘገቡ መልካም ተግባራት ተሞክሮዎች በማስፋት ክፍተቶችን በፍጥነት በማረም በቀጣይ የተሻለ ስራ ለመስራት የክትትልና የቁጥጥር ስራዎች ተጠናክረው እንዲሄዱ እየተሰሩ የሚገኙ ተግባራት አበረታች በመሆናቸው አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ተናግረዋል አስተያየት ሰጪዎቹ።
ዘጋቢ፡ ሪድዋን ሰፋ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
በተፈጥሮ የሚከሰተውን የመሬት መንሸራተት አደጋ ለመቀነስ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት ጥናትና ምርምር ለማድረግ ማቀዱን ገለፀ
አርብቶ አደሩን ከእንስሳት ሀብት ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ የእንስሳት ኤክስፖርት ማዕከላት እንደሚያስፈልጉ ተጠቆመ
በጌዴኦ ዞን የጤና መድህን አባል የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የይርጋ ጨፌ ከተማ አስተዳደር ጤና ጽህፈት ቤት አስታወቀ