በማህበር የተደራጁ ወጣቶች ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ወጣቶች የስራ ዕድል እየፈጠሩ መሆናቸውን ገለጹ

በማህበር የተደራጁ ወጣቶች ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ወጣቶች የስራ ዕድል እየፈጠሩ መሆናቸውን ገለጹ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 12/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በማህበር የተደራጁ ወጣቶች ከተማ አስተዳደሩ ያመቻቸላቸውን የስራ ዕድል በመጠቀም፥ ከራሳቸው አልፎ ለሌሎች ወጣቶች የስራ ዕድል እየፈጠሩ መሆናቸውን በስልጤ ዞን አለም ገበያ ከተማ የሚገኙ ኢንተርፕራይዞች ተናገሩ።

የአለም ገበያ ከተማ አስተዳደር ኢንተርፕራይዝ ዩኒት በበኩሉ የተለያዩ ገቢ ማስገኛ መስኮችን በመለየት ስራ አጥ ወጣቶችን እያሰማራና ውጤታማ እያደረጋቸው መሆኑን ገልጿል።

በከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ ዘርፎቾ ተሰማርተው እየሰሩ ካሉ ኢንተርፕራይዝ ማህበራት “ቢእዝኒላህ” የእንጨትና ብረታ ብረት አንዱ ሲሆን፥ ማህበሩ በ2015 ዓ/ም 360ሺ ብር መነሻ ወደስራ መግባቱን የተናገረው የማህበሩ ሰብሳቢ ወጣት እንዳለ ባሙድ፥ አሁን ላይ የማህበሩ ካፒታል ከ 7 ሚሊየን ብር በላይ መድረሱን አስታውቋል።

ማሕበሩ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የቤትና የቢሮ እቃዎችን በመስራት ለከተማው ማህበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ እንደሆነ ወጣት እንዳለ ተናግሯል።

ከተማ አስተዳዳሩ የመስሪያ ቦታ እና ብድር ከማመቻቸት ጀምሮ እያደረገላቸው ያለው ድጋፍ ለስራቸው ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋፆ እንዳለው የተናገረው ወጣቱ ማሕበሩ በአሁኑ ወቅት ለ32 ወጣቶች የስራ እድል መፍጠሩን ገልጸዋል።

“መደመር” ኢንተርፕራይዝ ማህበር በከተማው ተደራጀተው ከሚሰሩ ማሕበራት መካከል ሲሆን በወተት ላም እርባታ ላይ ትኩረት በማድረግ እየሰራ ባለው ስራ ተጠቃሚ መሆኑን ማህበሩ ሰብሳቢ ወጣት ሻሚል ሽፋ ተናግሯል።

ከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዳደረገላቸው የጦቆመው ወጣቱ፥ ድጋፉን በቀጣይ አስፍተው እንዲሰሩ የሚያነሳሳ ነው ብለዋል።

በከተማ አስተዳደሩ 3ሺ 250 ወጣቶች በተለያዩ የስራ ዘርፎች ተሰማርተው እየሰሩ መሆኑን የአለም ገበያ ከተማ አስተዳደር የኢኮኖሚ ክላስተር የኢንተርፕራይዞች ልማት ዩኒት ኃላፊ አቶ ኑረዲ ሸረፋ ተናግረዋል።

አብዛኞቹ ወጣቶች በማንፋክቸሪንግ፣ በግብርና በአገልግሎት ዘርፎች የተሰመሩ ናቸው ያሉት አቶ ኑረዲን ስራ አጥ ወጣቶችን ከመለየት ጀምሮ ወደ ስራ እስከ ማስገባት ድረስ መከናወኑን አስረድተዋል፡፡

ለስራቸው ውጤታማነት ከተለያዩ ተቋማት ብድር ከማመቻቸት ጀምሮ የመስሪያ ቦታ እና ሌሎችንም ድጋፎች ከተማ አስተዳደሩ እያደረገ ስለመሆኑ አቶ ኑረዲን አንስተዋል።

በተያዘው በጀት አመት ለ2ሺ 94 ወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር የታቀደ ሲሆን እስካሁን 398 ወጣቶች በተለዩ የስራ መስኮች መሰማራታቸውን ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ አሚና ጀማል – ከሆሳዕና ጣቢያችን