የመዘናጋቱን ችግር በመቅረፍ ህብረተሰቡ እራሱን ከኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ስርጭት ሊጠብቅ እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ

በክልሉ አዲስ ከተመረመሩ 200 ሺ ሰዎች ውስጥ 967 በቫይረሱ መያዛቸው ተጠቁሟል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት የ2017 በጀት ዓመት ዓመታዊ አፈጻጸምና እና የ2018 በጀት ዓመት 1ኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸም በገመገመበት ወቅት የተገኙት የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ምክትል የቢሮ ኃላፊና የጤና ፕሮግራሞች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኃይሌ ዘውዴ እንደተናገሩት፤ በክልሉ ለረጅም ዓመታት ዝቅተኛ አፈፃፀም ሲመዘገብበት የነበረው የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ምርመራ አገልግሎት በ2017 በጀት ዓመት 82 በመቶ የተከናወነና ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበት ነው።

በክልሉ ውስጥ 38 የጤና ተቋማት የኤች.አይ.ቪ ምርመራ እየሰጡ መሆኑን የተናገሩት አቶ ኃይሌ፤ በቀጣይ የተቋማቱን አሀዝ ከፍ የማድረግ ስራ ይሰራል ብለዋል።

በክልሉ 9 ሺ 20 ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ወገኖች ህክምናቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ ሲሆን በያዝነው በጀት ዓመት ተቋማትን በማስፋፋት ህክምናውን ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል።

እጥረት የሚታይባቸው ከእናት ወደ ልጅ ቫይረሱ እንዳይተላለፍ የሚደረገውን ጥረት በበጀት አመቱ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

በህብረተሰቡ ውስጥ የሚታየው መዘናጋት ተቀርፎ የመከላከሉን ስራ አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋልም ብለዋል አቶ ሀይሌ።

የክልሉ ጤና ቢሮ የኤች.አይ.ቪ መከላከል እና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ከሰሬ በበኩላቸው፤ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን ለመከላከል ከተቀመጡት ሶስት 95 አቅጣጫዎች ውስጥ አንዱ የሆነው እና ምርመራን በሚመለከት 200 ሺ ሰዎችን ለመመርመር ታቆዶ 92 ከመቶ መመርመር ተችሏል፡፡ በዚህም 967 ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው መገኘቱን ጠቁመዋል። ተመርምረው የተገኘባቸው ወደህክምና ከመውሰድ አንጻርም ጉድለት መኖሩን ተናግረዋል።

ከእናት ወደልጅ የሚተላለፈውን ከመከላከል አንጻር 77 ከመቶ በላይ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም ተጠናክሮ ቢቀጥል እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የተቀዛቀዘውን የማህበረሰብ ንቅናቄ ስራ የማስቀጠል ስራ አጠናክሮ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

በተለይም ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ተገቢ ክትትል ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በውይይቱ ላይ ከካፋ፣ ከሸካና ቤንች ሸኮ ዞኖች የመጡ የየዞኖቹ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሮች በበኩላቸው፤ በበጀት አመቱ እንደዞናቸው ኤች.አይ.ቪ የመከላከል ተግባር አጠናክረው መስራታቸውን ጠቁመዋል።

ነገር ግን ከንቅናቄ አንጻር ጉድለት መኖሩን ጠቁመው ህብረተሰቡን የማነቃነቅ እና የቅስቀሳ ስራ ተጠናክሮ መሰራት አለበት ብለዋል።

ቫይረሱ በደማቸው ያለ እና በተለያዩ በጎ አድራጎት ማህበራት ታቅፈው የሚሰሩ አስተያየት ሰጪዎች፤ የበሽታው ስርጭት በየእለቱ እየጨመረ ቢመጣም ግንዛቤ የመፍጠሩ ስራ በመቀዛቀዙ ዛሬም ስርጭቱን መግታት አልተቻለም ብለዋል። ስለዚህ የንቅናቄው ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።

በክልሉ በተደረገው የአፈጻጸም ግምገማም የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ዞኖች እና ተቋማት እውቅና ተሰጥቷል።

ዘጋቢ፡ አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን