ለዜጎች በክህሎትና በዝግጅት ላይ የተመሰረተ የስራ እድል መፍጠር መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑ ተገለጸ

ለዜጎች በክህሎትና በዝግጅት ላይ የተመሰረተ የስራ እድል መፍጠር መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ መስከረም 27/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ለዜጎች በክህሎትና በዝግጅት ላይ የተመሰረተ የስራ እድል መፍጠር መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው የ1ኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም የግምገማ መድረክ አካሂዷል።

የማእከላዊ ኢትዮጲያ ክልል ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ ከእቅድና ከፈፃሚ አካላት ዝግጅት ባሻገር የመጀመሪያው ሩብ አመት የስራ ፈላጊዎችና የፀጋ ልየታ የሚደረግበት መሆኑን አንስተዋል።

በገጠር ዘርፍ ከግብርና ጋር በተያያዘ የእርሻ ወቅትን መነሻ ያደረገ የስራ እድል የሚፈጠርበት በመሆኑ በሩብ አመቱ ለቀጣይ እቅድ መሳካት አመላካች የሆኑና የተሻሉ ስራዎች የተከናወኑበት ነው ብለዋል።

ከስራ ፈላጊ ልየታ አንፃር እስከ ነሃሴ ሰላሳ ለማጠናቀቅ ግብ ተጥሎ መሰራቱን ጠቅሰው ከ98 በመቶ በላይ ልየታ ማሳካት መቻሉንም ተናግረዋል።

በዚህ ሂደት ላይ የስራ ፈላጊ ልየታ ብቻም ሳይሆን የፀጋ ልየታም ጭምር በማድረግ የተለዩ ስራ ፈላጊዎች በየትኛው ዘርፍ የስራ እድል እንደሚፈጠርላቸውም በዝርዝር ማየት ተችሏልም ነው ያሉት።

በአንደኛው ሩብ አመት 20 በመቶ ለማሳካት ከታቀደው ተግባር አንፃር በዋና ዋና ተግባራት ላይ በተለይም ከልየታ፣ ከስራ ስምሪት፣ ከመሬትና ከፋይናስ አቅርቦት ጋር የተሻለ አፈፃፀም መታየቱንም አብራርተዋል።

በቀጣይ በትኩረት ሊሰራባቸው የሚገቡና በውስንነት የተነሱ ጉዳዩች መኖራቸውን ያወሱት አቶ ሙስጠፋ፥ ከዜጎች ምዝገባ፣ ከኢንተርፕራይዝ ምዝገባ፣ ዲጂታላይዝ ከማድረግ አኳያ እና ከሽግግር ጋር ተያይዞ ውስንነቶች መታየታቸውና በቀጣይ በትኩረት ሊሰራባቸው ይገባልም ብለዋል።

እንደ ክልል ከተያዘው በጀት ባሻገር በየደረጃው ያሉ መዋቅሮች ለዘርፉ መመደብ ያለባቸውን ፋይናንስ በወቅቱ በመመደብ የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል ሲሉም ተደምጠዋል።

በ2018 በጀት ዓመት በክልሉ ለ400 ሺ ስራ አጥ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ያስታወሱት ሃላፊው በዚህም 80 በመቶ ለሚሆኑት በቋሚነት መሆኑን አውስተው በሩብ አመቱ ከ60 በመቶ በላይ መፈፀሙን አብራርተዋል።

ዘላቂ የስራ እድል ከመፍጠር አንፃር በትኩረት የሚሰራበት ነው ያሉት አቶ ሙስጠፋ፥ በዚህ ረገድ በስራ ማእከላት ላይ አዳዲስ የሪፎርም እሳቤዎችን ተግባራዊ በማድረግ ስራዎች ከተሰሩ በአመቱ ለመፈፀም የተያዘውን ግብ ማሳካት እንደሚቻል የአንደኛ ሩብ አመቱ ተግባር አመላካች ነው ብለዋል።

የውጭ ሃገር ስራ ስምሪት አንዱ የስራ መፍጠሪያ አቅም ነው ያሉት አቶ ሙስጠፋ በእስካሁኑ ሂደትም ከ38 ሺህ በላይ ዜጎች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመናበብ የሚሰራ ስራ በመሆኑ በስራ ማእከላት ምዝገባ የፈፀሙና ሌበር አይዲ የወሰዱ ዜጎች በቴክኒክና ሙያዎችና ፈቃድ በተሰጣቸው ማሰልጠኛ ተቋማት ላይ ስልጠና ወስደው በምዘና ብቁ ሲሆኑ በህጋዊ መንገድ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት እድል ተጠቃሚ የሚሆኑበት እድል ይኖራል ብለዋል።

ለዜጎች በክህሎትና በዝግጅት ላይ የተመሰረተ የስራ እድል መፍጠር መሰረታዊ ጉዳይ በመሆኑ ለዚህም በተያዘው በጀት አመት ከ27 ተቋማት ጋር የጋራ መግባቢያ ስምምነት በመፈራረም እቅድ ታቅዶ በቅንጅት እየተሰራ እንዳለም አመላክተዋል።

በሌላ በኩል ከማስቆጠብና ብድር ከማስመለስ አኳያ በትኩረት እየተሰራበት መሆኑን በማንሳት በየሳምንቱ እየተገመገመ ይገኛል ያሉት ሃላፊው በዚህም መልካም አፈፃፀም መኖሩን አክለው አንዳድ መዋቅሮች ከነበረባቸው ውዝፍ እዳ ነፃ እየሆኑ ይገኛሉ።

አቶ ታምራት ተስፋሁን በቢሮው ምክትልና የከተማ ዘርፍ ስራ እድል ፈጠራ ሃላፊ በበኩላቸው በከተሞች የተፈጠሩ ኢኒሼቲቮች ለስራ እድል ፈጠራው ዘርፍ ትልቅ አበርክቶ እንዳለው በማንሳት ይህም በሩብ አመቱ ለመፈፀም ከታቀደው አንፃር እንደዘርፍ ከመቶ ፐርሰንት በላይ ማሳካት ተችሏልም ብለዋል።

ወቅቱ ለቀጣይ የተሻለ አፈፃፀም ለማከናወን ለዜጎች ምቹ ሁኔታዎች የሚፈጠርበት ነው ያሉት አቶ ታምራት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉም ብለዋል።

በቢሮው ምክትልና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ሃላፊ ወይዘሮ ዙልፋ አለዊ እንደገለጹት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ከግብርና ቀጥሎ ለሃገር ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት እንደሆነ ተደርጎ በልዩ ትኩረት እየተሰራበት ይገኛል።

በመሆኑም በተለይ በሃገር አቀፍ ደረጃ ባለፈው አመት የወረደው አዲሱን የገጠር ኢንዱስትራላይዜሽን ኢኒሼቲቭ መነሻ ባደረገ መልኩ ዘርፉ በከተማ ብቻ ሳይሆን በገጠር ደረጃም ውጤታማ የሆነ ተግባር እንዲያስመዘግብ ጠንካራ ስራዎች መሰራታቸውንም አንስተዋል።

የየዘርፉ ኃላፊዎች በዝግጅት ምዕራፍ የነበሩትን ጥንካሬዎችን በማጉላት እና የነበሩ ክፍተቶችን በማረም በቀጣይ ጊዜ የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ ሚፍታ ጀማል – ከወልቂጤ ጣቢያችን