ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ተገለጸ

ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ተገለጸ

ሀዋሳ፡ መስከረም 27/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በዞኑ ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ተለይተው ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን የጉራጌ ዞን ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ አስታወቀ።

የጉራጌ ዞን ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ በ2017 ዓ.ም አፈጻጸምና በ2018 ዓ.ም ዕቅድ ላይ ያተኮረ የሴክተር ጉባኤ በወልቂጤ ከተማ አካሄዷል።

በመድረኩ ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ልዩ አማካሪ አቶ ዳርጌ ተክሉ፥ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ብዙ ተልዕኮዎችን ይዞ የሚሰራ ተቋም መሆኑና ዘርፉ ላይ አጋዥ አካላትን በማሳተፍ ተቋሙን በአግባቡ ማደራጀትና ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።

በተለይም ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመቀነስ የስራ ባህልን በማሳደግና በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የተጀመሩ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል።

ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማገዝ በዘላቂነት ራሳቸው የሚመሩበትና ማህበራዊ መስተጋብራቸው በሚያጠናክሩበት መንገድ መሆን እንዳለበትና ለዚህም ማህበረሰቡና ባለሀብቱን በማስተባበር መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የጉራጌ ዞን ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ አቶ መኩሪያ ተመስገን እንዳሉት በመምሪያው ድጋፍ የሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎችን በመለየት የግንዛቤና የአይነት ድጋፍ መደረጉና በዚህም ወላጅ አጥ ህጻናት፣ የአካልና የአእምሮ ጉዳት፣ የኢኮኖሚ አቅም ውስንነት ያለባቸውና ሌሎችም ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በአሰሪና ሰራተኛ ዘርፍ በዋናነት የሰው ሀብት ፍላጎትና አቅርቦትን ለማጣጣም የሚያስችል የስራ ገበያ መረጃ ስርኣት የመዘርጋትና መተግበር፣ የስራ ስምሪት አገልግሎት በማስፋፋት የአሰሪና ሰራተኞች ማህበር በማደራጀት ግዴታቸውን ለመወጣትና መብታቸውን ለማስከበር የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ነው ያሉት አቶ መኩሪያ።

በበጀት ዓመቱ በማህበረሰብ አቀፍ ድጋፍና እንክብካቤ ጥምረት አማካኝነት በአይነትና በጥሬ ገንዘብ ከ21 ሚሊየን ብር በላይ በማሰባሰብ ከ9 ሺ በላይ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ሲሉ አብራርተዋል።

በዚህም 43 ድርጅቶች ማህበራዊ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ በማድረግ 142 የአካል ጉዳተኞች በተለያዩ የስራ መስኮች ማሰማራት መቻሉን አስታውቀዋል።

ለአካል ጉዳተኞች የዊልቸር ድጋፍ፣ የአካል ጉዳተኞችና የኣረጋዊያን ማህበርን መደገፍ፣ የህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከልና የኢኮኖሚ አቅም ውስንነት ያለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ እንዲሁም የግንዛቤ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየትም በዞኑ ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ የሚከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ገልጸው የተሻለ ስራ ለመስራት የሚደረጉ የግንዛቤና የአይነት ድጋፎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው።

በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ከትምህርት ቤት ጀምሮ በሁሉም አካባቢዎች የግንዛቤ ስራዎችን በመስራትና ከአሰሪና ሰራተኛ ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ሌሎች ሴክተር መስሪያ ቤቶች አጋዥ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

በመጫረሻም የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ መዋቅሮችና ባለዳርሻ አካላት እውቅና የተሰጣቸው ሲሆን በ2018 ዓ.ም ለሚከናወኑ ተግባራት የግብ ስምምነት ተፈራርመዋል።

በመድረኩ ከዞን፣ ከወረዳና ከከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ አካላት ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡ መላኩ ንማኒ – ከወልቂጤ ጣቢያችን