“የጋራ ርብርብ ለላቀ ትምህርት ጥራት” በሚል መሪ ቃል የኮንታ ዞን ትምህርት መምሪያ የ2018 ዓ.ም የትምህርት ጉባኤውን አካሄደ
ሀዋሳ፡ መስከረም 27/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በኮንታ ዞን ትምህርት መምሪያ የ2018 ዓ.ም የትምህርት ጉባኤ “የጋራ ርብርብ ለላቀ ትምህርት ጥራት” በሚል መሪ ቃል ተካሂዷል።
በጉባኤው የተገኙት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታከለ ተስፉ ትምህርት ለአንድ ሀገር ዕድገት የማይተካ ሚና እንዳለው ገልፀው፥ ለዚህም ትናንትን የሚናገር፣ ዛሬን የሚገልጥና ነገን የሚያልም የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት በትምህርት ላይ በልዩ ትኩረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
የትምህርት ስራ አቅም የሚጠይቅ፣ ብዙ ሀብት የሚፈልግና ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል እንዲሁም የማያቋርጥ ትግል የሚጠይቅ በመሆኑ ያለንን አቅም አሟጦ በመጠቀም የትምህርት ስራ ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባ አስረድተዋል።
በሀገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ መትጋትና የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ባለድርሻ አካላትና መላው ማህበረሰብ የበኩላቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።
በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ም/ል ኃላፊና የስርዓተ ትምህርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አባተ ኡቃ የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ የሚያስችሉ የተለያዩ አሰራሮች እየተዘረጉ መሆኑን አንስተው የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ሁሉም ባለድርሻ አካለት መረባረብ እንደሚገባ አመላክተዋል።
የትምህርት ስብራትን ለመጠገን ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ትኩረት ማደረግ እንደሚገባ ጠቁመው፥ በተጀመረው ጉዞ የተሻላ ለውጥ እንዲመጣ ከላይ ጀምሮ ድጋፍ እና ክትትል ሥራዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
የዞኑ ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ገዛኸኝ ገዝሙ ትምህርት ህብረተሰቡ የተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዕድገት ለማምጣት መሠረታዊ መሆኑን ገልፀው በትምህርት ለትውልድ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚገባ አስረድተዋል።
የትምህርት ሴክተሩ አመራሮችና ባለሙያዎች ቅንጅታዊ ስራዎችን ማጠናከር፣ ለስራው ልዩ ትኩረት መስጠት፣ በትምህርት ስራ ላይ ብቻ ማተኮርና ድጋፍና ክትትል ማሳደግ እንደሚገባ ያስገነዘቡት አቶ ገዛኸኝ፥ የውስጥ ገቢ አቅምን ማሳደግና በተማሪ ስነ ምግባር ላይ መስራት ይገባል ነው ያሉት።
የኮንታ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አጥናፉ አበራ ትምህርት በዕውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት የተገነባ ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ ማፍራት የትምህርት ሴክተር ተልዕኮ መሆኑን ገልጸው፥ ከዚህ መነሻ ባለፉት ዓመታት የትምህርት ጥራትና ተገቢነት ማረጋገጥ፣ የትምህርት ተደራሽነትና ተሳትፎ ማሳደግ፣ የትምህርት ብክነት መቀነስ፣ በትምህርት ተቋማት መልካም አስተዳደር ማስፈንና መሠል ስራዎች በትኩረት መከናወናቸውን ገልፀዋል።
በሂደቱ የሚስተዋሉ የወላጆች ክትትል ማነስ፣ የመምህራን ብቃት ማነስ፣ የመማሪያ ቁሳቁስ እጥረት፣ የተማሪዎች ትኩረት ማጣት፣ ኢኮኖሚያዊና መሠል ችግሮች ያጋጠመውን የትምህርት ስብራት ለመጠገን አዳጋች እንዳደረጉ የጠቆሙት ኃላፊው፥ በቀጣይም የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ ውጤታማ ለመሆን እየተሰራ እንደሚገኝ በማንሳት የሁሉም አካላት ርብርብ እንደሚያሻ አስረድተዋል።
ዘጋቢ፡ ብርሃኑ ግንባቶ – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
አቶ ጌታቸው ኬኒ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብሄረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ሆነው ተሾሙ
ባለፉት ጊዜያት በህዝብና በመንግስት መካከል ያለውን ግንኙነት ያጠናከሩ ተግባራት መከናወናቸውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ገለጸ
የኮሪደር ልማት ሥራ ከተማን ዉብ፣ ሳቢና ለነዋሪዎች ምቹ ከማድረግ ባለፈ ለበርካታ ወጣቶች ሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን የዳዉሮ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ አስታወቀ