ከ6ሺህ በላይ ከብቶችን ዝርያ ለማሻሻል ዕቅድ መያዙ ተገለጸ

ከ6ሺህ በላይ ከብቶችን ዝርያ ለማሻሻል ዕቅድ መያዙ ተገለጸ

በባስኬቶ ዞን በያዝነው የምርት ዘመን ከ6ሺህ በላይ ከብቶችን ዝርያ ለማሻሻል ዕቅድ መያዙን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

መምሪያው ዞናዊ የላሞችና ጊደር በሆርሞን ማድራትና ማዳቀል የሲንክሮናይዜሽን ዘመቻ በቦላ ጋባላ ቀበሌ አስጀምሯል።

በባስኬቶ ዞን ከ420 ሺህ በላይ የዳልጋ ከብቶች እንደሚገኙ ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ የሚያመላክት ሲሆን፥ ነገር ግን የብዛታቸውን ያክል ምርታማ እንዲሆኑ ለማስቻል ዝርያቸውን የማሻሻል ሥራ ከጊዜ ወደ ጊዜ በልዩ ትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተመላክቷል።

ከመደበኛው ጎን ለጎን ላሞችና ጊደሮችን በሆርሞን ማድራትና ማዳቀል የሲንክሮናይዜሽን ዘመቻ በዞኑ ቦላ ጋባላ ቀበላ የተጀመረ ሲሆን፥ በዘመቻው ከ1ሺህ በላይ ከብቶችን ለማዳቀል ዕቅድ መያዙን የዞኑ ም/አስተዳዳሪና ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ወንዳፍራሽ ንጉሤ ገልጸዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ኢ/ነር ፍሻለው በበኩላቸው የዘመቻ ሥራው ይፋ የደረገበት የቦላ ጋባላ ቀበሌ በመኖ ልማትና በእንስሳት ዕርባታ በሞዴልነት ከሚጠቀሱ የዞኑ ቀበሊያት አንዱ መሆኑን ተናግረው ይንን ተሞክሮ ማስፋት ይገባል ብለዋል።

በዞኑ የተለያዩ የግብርና ዕድገት ፕሮጀክቶች ለግብርናው ዘርፍ እድገት ሰፋፊ ድጋፎችን እያደረጉ መሆናቸውን ያነሱት አስተዳዳሪው፥ በዕለቱ ወደ ሥራ የገባውን ዘመናዊ የከብቶች በረት ሰርቶ ላስረከበው FSRP ፕሮጀክት ምስጋና አቅርበዋል።

የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ሥራው ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን የተሻሻለ የእንስሳት መኖ ልማት ልዩ ትኩረት የሚሻ መሆኑን የግብርና መምሪያ ኃላፊው አቶ ወንዳፍራሽ አሳስበዋል።

የግብርና መምሪያ መኖ ልማት ቡድን መሪ አቶ በኃይሉ መንግስቱ እንደገለጹት በምርት አመቱ 1 ሺህ 810 ሄ/ር መሬት በመኖ ለመሸፈን ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመው፥ በሩብ አመቱ ከ810 ሄ/ር በላይ መሬት በተለያዩ የመኖ ቁርጥራጮች ማልማት መቻሉን ገልጸዋል።

በድቀላ መርሐ ግብሩ ከብቶቻቸውን ይዘው ከመጡ የአካባቢው አርሶ አደሮች መካከል አርሶ አደር ዶሮ ዶዶ እና ተሾመ ተሻለ ላሞችንና ጊደሮችን በተሻሻለ ዝርያ ማዳቀል ከጀመሩ ወዲህ ተጠቃሚነታቸው መጨመሩን ተናግረው ከብቶቹ ለሆርሞኑ ምላሽ በሚሰጡበት ወቅት አዳቃይ ባለሙያው በወቅቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

የባስኬቶ ዞን ላስካ ዙሪያ ወረዳ እንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር ኤፍሬም ገረሱ በዕለቱ የተሠጠው ማነቃቂያ ሆርሞን እንጂ የድቀላ ፈሳሽ ባለመሆኑ ለሚቀጥሉት ተከታታይ ቀናት ከብቶቹ ምልክት ሲያሳዩ በተገቢው ሁኔታ ለማዳቀል አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል።

ዘጋቢ: አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን