‎‎የጂንካ ዩኒቨርስቲ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍና እገዛ እንደሚያስፈልግ ገለጸ

‎‎የጂንካ ዩኒቨርስቲ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍና እገዛ እንደሚያስፈልግ ገለጸ

ሀዋሳ፡ መስከረም 26/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ዩኒቨርስቲው እንደሀገር የተሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡ በመዋጣት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ባለድርሻ አካላት ድጋፍና እገዛ እንደሚያስፈልግ የጂንካ ዩኒቨርስቲ አስታወቀ።

‎ዩኒቨርስቲው ከአሪ ዞንና ደቡብ ኦሞ ዞን የማህበረሰብ ተወካዮች ጋር የጋራ ምክክር አድርጓል።

‎በዩኒቨርስቲው መማር ማስተማር፣ በምርምና በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራትና በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ዙርያ ሰነድ ቀርቦ ውይይት በማድረግ ለተነሱ ሃሳብና አስተያየት ምላሽና ማብራርያ ተሰጥቷል።

‎የጂንካ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዮሐንስ ይትባረክ ዩኒቨርስቲው ባለፉት አመታት በ3ቱ ዋና ዋና ተግባራት በርካታ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ገልፀው፥ እንደሀገር የተሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡ በመወጣት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍና እገዛ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

‎አክለውም በዩኒቨርስቲው ሪፎርም ከተደረገ በኋላ ከአካዳሚክና አስተዳደር ዘርፍ ሰራተኞች ጋር የተለያዩ ውይይቶች መካሄዳቸውን ጠቁመው፥ ከሁለቱ ዞኖች የማህበረሰብ ተወካዮች ጋር የተደረገው ውይይት በቀጣይ ለሚሰሩ ስራዎች ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።

‎በዩኒቨርስቲው የአካዳሚክ ምርምና ቴክኖሎጂ ሽግግር ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ተስፋዬ አለሙ በውይይቱ ወቅት የትምህርት ስብራትን ለመጠገን የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን መደገፍ፣ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ማጠናከር፣ የአቅም ግንባታ ስራዎችን መስራት፣ በጥናትና ምርምር በየአከባቢው የሚፈጠሩ ግጭቶች መፍታት፣ በግብርናው ዘርፍ የማህበረሰቡን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ይበልጥ ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል ።

‎የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የጂንካ ዩኒቨርስቲ ቦርድ አባል አቶ አብረሃም አታ በበኩላቸው፥ ዩኒቨርስቲው ባለፉት አመታት በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን ችግር በመለየት በምርምር የታገዙ ለማህበረሰቡ የሚጠቅሙ አበረታች ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ገልፀው፥ ይህንን አጠናክሮ በማስቀጠል ዩኒቨርስቲው ተወዳዳሪ እንዲሆን ከጎኑ በመሆን ማገዝና መደገፍ እንደሚገባ ተናግረዋል ።

‎የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ በበኩላቸው የጋራ ሀብት የሆነው የጂንካ ዩኒቨርሲቲን በመደመርና በመቀናጀት ለውጥ ለማምጣት አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ተናግረው ዩኒቨርስቲው የዳሰነች ማህበረሰብ በኦሞ ወንዝ ሙላት ከሚደርስበት ጉዳት ለመታደግ የሚያደርገውን ድጋፍና እገዛ አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበትና ሌሎች የባለድርሻ አካላትም የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ዘጋቢ፡ በናወርቅ መንግስቱ – ከጂንካ ጣቢያችን