ሀዋሳ፡ መስከረም 26/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከመደበኛ ትምህርት ቤቶች በተጨማሪ አዳሪ ትምህርት ቤት የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ረገድ ትልቅ ሚና እንዳለው የኮንታ ዞን ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡
“በአላማችን ላይ ትኩረት በማድረግ ጠንክረን ከሰራን ውጤታማ መሆን ይቻላል” ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡ የኮንታ ዞን የእሞታ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተናግረዋል፡፡
ከተማሪዎቹ መካከልም የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሳሙኤል አስራት፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ብቁና ተወዳዳሪ ለመሆን ከወዲሁ ጠንከሮ በመስራት፣ የመምህራኑ እና የወላጆቹ እገዛ ታክሎበት ለውጤት ለመብቃት ውስን ተማሪዎች በተመረጡ መምህራን በተሻለ ቦታ ቀን ሙሉ መማር ለትምህርት ጥራት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላኛዋ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ረድኤት ታደለ ልዩ የአዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ የመማር ዕድል ማግኘቷ ጊዜዋን በአግባቡ እንድትጠቀም ያስቻላት በመሆኑ የተለያዩ የመልመጃ ጥያቄ በመምህራን መሰራቱና ግልጽ ያልሆኑ ጥያቄዎችን ለመረዳት በአንድ ግቢ መሆኑ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግራለች።
ተማሪዎቹ በትምህርት ቤት ቆይታቸው ከመምህራን በሚሰጠው ድጋፍ ተጨማሪ ትጋትና ጥረትን በማከል ውጤታማነታቸውን ለማስቀጠል ከአቻቸው ጋር የንባብ ጊዜ በማሳለፍ ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ ከወዲሁ እየተዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዓላማችን ላይ ትኩረት በማድረግ ጠንክረን ከሰራን፤ የመምህራን እገዛና የወላጆች ክትትል ከታከለበት ከፍተኛ ውጤት ከማምጣት የሚያግድ ነገር አለመኖሩን ተማሪዎቹ ተናግረዋል።
ከት/ት ቤቱ መምህራን መካከል የኬሚስትሪ መምህር ማቱሳላ ወሰን እና የባዮሎጂ መ/ር ሚሊዮን ዘሪሁን በትምህርት ቤቱ የተማሪዎች ውጤት እንዲሻሻልና የትምህርት ጥራት እንዲጠበቅ የተለያዩ የማስተማሪያ ስነ ዜዴዎችን ተግባራዊ እያደረጉ መሆናቸውን አመልክተዋል።
የእሞታ ልዩ ት/ት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋሁን ሰበቡ ት/ት ቤቱ በ2016 ዓ/ም በ8ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት ያመጡትን ተማሪዎች በመመልመልና የመግቢያ ፈተና በመስጠት በፈተናው የተሻለ ውጤት ያመጡትን ተማሪዎች በመቀበል የተጀመረ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ሰዓት 65 ተማሪዎችን ተቀብሎ ከ 9ኛ እስከ 11ኛ ክፍል እያስተማረ የሚገኝ ሲሆን በቀጣይም የቅበላ አቅም እና ውጤታማነትን በማሻሻል በሀገር አቀፍ ደረጃ የምሁራን መፍለቅያ እና ግንባር ቀደም ተቋም የማድረግ ግብ በመያዝ እተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የትምህርት አሰጣጡን በማጠናከር፣ ለተማሪዎች የሚደረገውን ድጋፍ በማሻሻልና የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ በአገር አቀፍ ፈተና ተወዳዳሪ ሆነው እንዲገኙ የሁሉም ተማሪዎችን መጠነ ማለፍ በማሳደግ በ12ኛ ከፍል ተፈታኞች መካከል 75% እና ከዚያ በላይ በማምጣት ጥሩ ውጤት አስመዝግበው ሁሉም ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ እንዲገቡ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በዞኑ የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የተጀመረው ስራ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እያሳየ ነው ያሉት ደግሞ የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አጥናፉ አበራ ናቸው።
ከመደበኛ ትምህርት ቤቶች በተጨማሪ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ማስፋፋት የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ እና አቅም እያላቸው እድሉን ላላገኙ ተማሪዎች ትልቅ እድል በመሆኑ የእሞታ አዳሪ ትምህርት ቤት ለአካባቢው ትልቅ ዕድል ይዞ የመጣ ነው ብለዋል።
ትምህርት ቤቱ ብቁና በአገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ተማሪዎች የሚፈልቁበት እንዲሆን በተቀናጀ መንገድ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸው የተጣለበትን ሀላፊነት እንዲወጣም ድጋፍ እና ክትትል ይደረጋል ነው ያሉት።
ትምህርትን ያለ ህዝባዊ ድጋፍ ውጤታማ ማድረግ አይቻልም ያሉት ኃላፊው ትምህርት ቤቱ ሀላፊነቱን በብቃት እንዲወጣ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ረገድ ባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁሟል።
ዘጋቢ፡ ፋሲካ ሙሉጌታ – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
አቶ ጌታቸው ኬኒ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብሄረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ሆነው ተሾሙ
ባለፉት ጊዜያት በህዝብና በመንግስት መካከል ያለውን ግንኙነት ያጠናከሩ ተግባራት መከናወናቸውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ገለጸ
የኮሪደር ልማት ሥራ ከተማን ዉብ፣ ሳቢና ለነዋሪዎች ምቹ ከማድረግ ባለፈ ለበርካታ ወጣቶች ሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን የዳዉሮ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ አስታወቀ