የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መቆየቱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አለማየሁ ባውዲ ገለፁ

‎በምክር ቤቱ 6ኛ ዙር 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የማስጀመሪያ ጉባኤ ላይ መግለጫ ተሰጥቷል።

‎ደቡብ ኢትዮጵያ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አለማየሁ ባውዲ በመግለጫቸው፤ የህብረ ብሔራዊነትና የብዝሃ ብሔር ማዕከል የሆነችውን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሲሠራ መቆየቱን ገልፀው 6ኛ ዙር 2ኛ የሥራ ዘመን ማስጀመሪያ ጉባኤ ሁለቱም የህዝብና የብሔረሰቦች የምክር ቤት አባላት በተገኙበት መስከረም 30 ቀን 2018 ዓ.ም በአርባ ምንጭ ባህል ማዕከል እንደሚካሄድ አብራርተዋል።

‎በመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተገኝተው ሁለቱም ምክር ቤቶች ሥራ መጀመራቸውን የሚያበሰሩ ሲሆን የክልሉን መንግስት የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫም እንደሚቀመጥ አፈ ጉባኤው አስረድተዋል።

‎ክልሉ ከተመሠረተ ጀምሮ የክልሉን የህዝብ ጥያቄ ለመመለስ በርካታ ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመው ክልሉ ከተመሠረተ ጀምሮ የተመዘገቡ ስኬቶችን ይበልጥ ለማስቀጠልና ተግዳሮቶችንና ጉድለቶችን የዕቅድ አካል አድርጎ አቅጣጫ የሚቀመጥበት መሆኑን ገልፀዋል።

‎የህዝብን ተጠቃሚነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን በመግለጫቸው የገለፁት አፈ ጉባኤው፤ የመንግስት አቅጣጫዎችም በርዕሰ መስተዳድሩ እንደሚቀመጡ አብራርተዋል።

‎ጉባኤው የዚህን ዓመት ውጤታማነት የሚረጋገጥበት በመሆኑ መላው ህዝብ በአጽንኦት እንዲከታተል መክረዋል።

‎መስከረም 30 ቀን 2018 ዓ.ም የሚጀመረው የምክር ቤቶች ጉባኤ ላይ የሁለቱም ምክር ቤት አባላት፣ የክልል አመራሮችና መሪዎች፣ የሥራ ኃላፊዎች፣ ከ12ቱ ዞኖች የተውጣጡ አስተዳደር አካላት፣ 3ቱ የረጅኦ ፖልስ ከተማ አመራሮች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች እንዲሁም የተለያዩ ባለድርሻ አካላትና ተጋባዥ እንግዶች የሚገኙበት ይሆናል ብለዋል።

‎ዘጋቢ፡ አበበ ዳባ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን