የ2017 በጀት ዓመት የሴቶችን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንጻር በክልሉ የተሻለ ውጤት የተመዘገበበት እንደነበር የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ
ቢሮው ያለፈውን በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2018 ዕቅድ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቦንጋ ከተማ ገምግሟል።
የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ገነት መኩሪያ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ባለፈዉ በጀት ዓመት የሴቶች ተጠቃሚነትን በሁሉም ዘርፎች ለማረጋገጥ እንደ ክልል የተከናወኑ ተግባራት ስኬታማ ነበሩ።
ሴቶች ለሰላም እሴት ግንባታ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ያነሱ የቢሮ ኃላፊዋ በዚህ ረገድ በክልሉ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል።
የሴቶችን ቁጠባ ባህል ማሳደግ፣ በልማት ቡድኖች አደረጃጀቶችን ማጠናከርና መሰል ተግባራትንም ለአብነት አንስተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በግንዛቤ ላይ በትኩረት በመሰራቱ በግብርናው ዘርፍ የሴቶችን ተሳትፎ በማሳደግ በምግብ ራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሴቶች አወንታዊ ሚና እየተወጡ ይገኛሉ ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በወጣቶች በኩል አደንዛዥ ዕጾችንና መጤ ባህሎችን በንቅናቄ በመምራት ለውጥ ማስመዝገብ እየተቻለ መምጣቱን ተናግረዋል።
በክልሉ የህጻናትን መብት ለማስከበር በተደረጉ ጥረቶች የልደት ሰርተፊኬት መስጠት፣ የወላጅነት ማረጋገጫ መስጠት፣ የጉልበት ብዝበዛና ህገወጥ ዝውውር ከመከላከል አንጻር የተሻለ ወጤት እንደነበረም አስታውቀዋል።
በሌላ በኩልም የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከማሳደግ አንጻር ከብድር ስርጭትና ከስራ ዕድል ፈጠራ አንጻር የታዩ ክፍተቶችን ለማስተካከል በአስር ዓመቱ መሪ ዕቅድ ዉስጥ በማካተት በልዩ ትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል።
በመድረኩ ከተሳተፉት መካከል የቤንች ሸኮ ዞን ሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ሀላፊ ወ/ሮ ፀጋነሽ ሺታዬና የዳውሮ ዞን ሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ምክትል ሀላፊ አቶ ታምሩ ግዛው በ2017 ሴቶች፣ ህፃናት እና ወጣቶችን በተለያዩ ዘርፎች ተጠቃሚ ለማድረግ መሰራቱን ገልፀዋል።
በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጎጅ ልማዳዊ ድርጊትን መከላከልና የልማት ቡድኖችን በማጠናከር በየጊዜው ተጠቃሚነታቸውን ማሻሻል እየተቻለ መምጣቱን ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፡ ምኞት ወ/ሚካኤል – ከቦንጋ ጣቢያችን
More Stories
ጃፓን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ብራዚልን አሸነፈች
ከተሞች በዲጂታል ቴክኖሎጂ ታግዘው አገልግሎት መሥጠታቸው የተገልጋይና የአገልጋይ ግንኙነት ጤናማና እርካታ የተሞላበት እንዲሆን የሚያስችል መሆኑ ተገለጸ
አቶ ጌታቸው ኬኒ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብሄረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ሆነው ተሾሙ