የጂንካ መምህራን ብድርና ቁጠባ ህብረት ሥራ ማህበር የኢኮኖሚ አቅሙን በማሳደግ እየሠራ መሆኑን አስታወቀ

ሀዋሳ፡ መስከረም 25/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የጂንካ መምህራን ብድርና ቁጠባ ህብረት ሥራ ማህበር የተለያዩ አማራጮችን በማስፋት የኢኮኖሚ አቅሙን በማሳደግ እየሠራ መሆኑን ገለጸ።

ማህበሩ 22ኛውን ዓመታዊ ጉባኤ በጂንካ ከተማ አካሂዷል።

እስከ ሰኔ 30/2017 ዓ/ም ድረስ ማህበሩ 27 ሚሊዮን 984 ሺህ ብር ካፒታል እንዳለው እና በዚህም 296 አባላት ማፍራት መቻሉን የማህበሩ ሰብሳቢ አቶ ዘላለም ጌታቸው ገልፀዋል።

መምህራን በትውልድ ላይ እየሠሩ ያሉት ተግባር ወሳኝ መሆኑን የጠቀሱት የጂንካ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሲሳይ ጋልሺ፥ የመምህራን ኢኮኖሚ አቅም ከፍ እንዲል በማህበር በማደራጀት በኢንቨስትመንት ማዕቀፍ አስገብቶ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

በዚህም የቁጠባ አድማሱን በማሳደግ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፍ መምህራን ተሳትፎ አድርገው መንግስት መሬት አመቻችቶ ወደ ሥራ እንዲገቡ የዘርፉ አሠራር የሚፈቅድ ነው ሲሉም አቶ ሲሳይ ተናግረዋል።

ወደ ፊት ሥራው ውጤታማ በሚሆንበት ወቅት መሬት አቅራቢው መንግስትና በማህበር የተደራጁ መምህራን ከሚገኘው ገቢ የሚከፋፈሉበት ስሌት መቀመጡን ከንቲባው አስረድተዋል።

መምህራን የመማር ማስተማር ሥራ አጠናክረው በማስቀጠል ለውጤት እንዲሰሩ በዚህ ወቅት አሳስበዋል።

የማህበሩ አባላት በቁጠባ ማህበራዊያ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ማግኘታቸውን ገልፀዋል።

ማህበሩ በቀጣይ በጂንካ ከተማ ሁለገብ አገልግሎት መስጠት የሚችል ዘመናዊ ህንፃ ለመሥራት ዕቅድ ጨርሶ ወደ ተግባር እየገባ መሆኑን የማህበሩ ሰብሳቢ ገልፀዋል።

ማህበሩን ከዚህ በፊት ስመሩ የቆዩና የምርጫ ጊዜያቸው የተጠናቀቀባቸው አመራሮች በአዳዲሶች ተተክተዋል።

የማህበሩ የ2018 ዓ/ም ዕቅድም ቀርቦ ውይይት ከተደረገ በኋላ ፀድቋል።

ዘጋቢ: ተመስገን አበራ -ከጂንካ ጣቢያችን