ዞኑ ያለውን ከፍተኛ የኢኮኖሚ አቅም ያህል በተገቢው ሁኔታ ጥቅም ላይ አለመዋሉ ተገለጸ
ለመጀመሪያ ጊዜ የጌዴኦ ኢኮኖሚ እድገት ፎረም በዞኑ ዲላ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት እንደተናገሩት፤ የኢኮኖሚ ፎረሙ በዞኑ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተካሄደ ያለ ነው፡፡
ዞኑ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አቅም ያለው ቢሆንም በተገብው ሁኔታ ሳንጠቀም ቆይተናል ያሉት አስተዳዳሪው፤ ለአካባቢው ችግር አካባቢያዊ መፍትሄን ለመቅረጽ እየተካሄደ ያለ ፎረም መሆኑን አስታውቀዋል።
በቡና ኢኮኖሚ ባለፉት መቶ ዓመታት የዞኑ አርሶ አደሮች በቡናው ልማት ዘርፍ ተሠማርተው ቢቆዩም በቡናው ዘርፍ አልቀን ባለመሄዳችን በበቂ ሁኔታ ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆን አልተቻለም ብለዋል።
በቡና እሴትን ጨምሮ ከፍተኛ ትስስር ፈጥሮ ለዓለም ገበያ በማቅረቡ በኩል ያለው ሥራ የዳበረ ያለመሆኑ ለችግሩ ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል።
የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥም የእንሰት ምርት በዞኑ ሌላኛው የኢኮኖሚ ምንጭ ቢሆንም እስካሁን በአርሶ አደሩ ዘንድ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጡ በኩል መሻገር አለመቻሉንም ገልጸዋል።
የተለያዩ የኢኮኖሚ አማራጮች ባለቤት በሆነው የጌዴኦ ዞን ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ፎረሙ ማስፈለጉን የገለጹት ዶ/ር ዝናቡ፤ ለአካባቢያዊ ችግር አካባቢያዊ መፍትሔን በመቅረጽ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
አካባቢውን መቀየር ሀገርን መቀየር በመሆኑ ያሉ ምቹ ሁኔታዎችን በመጠቀም ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲሳተፉ አስተዳዳሪው ጠይቀዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የዕለቱ ክቡር እንግዳ ዶ/ር አበባየሁ ታደሰ በበኩላቸው፤ አንድ አካባቢ ለመልማት የራሱ የሆኑ ጸጋዎች አሉት ብለው የጌዴኦ ዞንም ለመልማት በርካታ ጸጋዎች ያሉት በመሆኑ ተሳታፊዎች ሀሳብ፣ ሀብትና ጉልበትን በማዋጣት እንዲሰሩ አሳስበዋል።
ባሉን ጸጋዎች በተሻለ ፍጥነት ምክክር የምናደርግበት ፎረም ነው ያሉት ርዕሰ መስተደድሩ፤ የጋራ መግባባትን ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል።
ሁላችንም በየሙያችን ካዋጣን አካባቢው ለመለወጥ ትልቅ ዕድል አለው ነው ያሉት ዶ/ር አበባየሁ፤ ሁላችንም የልማት አንባሳደሮች ሆነን የምንወጣበት መሆን አለበት ሲሉ ገልጸዋል።
ዘጋቢ: እስራኤል ቅጣው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
ጃፓን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ብራዚልን አሸነፈች
ከተሞች በዲጂታል ቴክኖሎጂ ታግዘው አገልግሎት መሥጠታቸው የተገልጋይና የአገልጋይ ግንኙነት ጤናማና እርካታ የተሞላበት እንዲሆን የሚያስችል መሆኑ ተገለጸ
አቶ ጌታቸው ኬኒ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብሄረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ሆነው ተሾሙ