በሀገር እና ዓለም አቀፍ ደረጃ በጥምርታ ለሚሰሩ የምርምር ሥራዎች እውቅና መስጠት እንደሚገባ የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ

በሀገር እና ዓለም አቀፍ ደረጃ በጥምርታ ለሚሰሩ የምርምር ሥራዎች እውቅና መስጠት እንደሚገባ የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ

‎የፕሮጀክት እና የህትመት ቀን “የምርምር፣ የፕሮጀክት እና የሕትመት ውስጥ ስኬቶችን ማክበር” በሚል መሪ ሀሳብ በአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ እየተከበረ ይገኛል፡፡

‎በዕለቱ መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኢንጂነር አብደላ ከማል እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ መጠን የምርምር ውጤቶችን ሸልፍ ላይ ከማስቀመጥ ባለፈ ለህብረተሰቡ ችግር ፈቺ ሆነው እንዲሰሩ የቀኑ መከበር የሚያነሳሳ ነው።

‎ዩኒቨርሲቲዎች የሚለኩትና እውቅና የሚያገኙት በሚሰሩት የምርምር ውጤቶች መሆኑን ዶ/ር ኢንጂነር አብደላ ተናግረው፤ በሀገር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በጥምርታ ለሚሰሩ የምርምር ሥራዎች እውቅና መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።

‎ዩኒቨርሲቲው በምርምር ሥራ መድረስ ወደሚፈልገው ደረጃ አለመድረሱን ጠቁመው፤ ይህንን ከፍ ለማድረግ የምርምር ሥራዎችን ለሚያከናውኑ መምህራን እውቅና በመስጠት ለማነሳሳት መሆኑን ተናግረዋል።

‎ፕሬዝዳንቱ አክለውም ጥናት አቅራቢዎች በፕሮጀክቶች እንዲሳተፉ እናበረታታለን ብለው፤ ከ2018 በጀት ዓመት ጀምሮ የምርምር ውጤቶች ማሳተም ለሁሉም ግዴታ መሆኑን ጠቁመዋል።

‎በዕለቱም በፕሮጀትና ህትመት ሥራዎች ዙሪያ ፓናል ውይይት የሚደረግ ሲሆን በ2017 በጀት ዓመት የፕሮጀክት ሥራዎችን ላሸነፉና በርካታ ሥራዎችን ላሳተሙ ተመራማሪዎች እውቅና ይሰጣልቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

‎በመርሀ-ግብሩ የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኢንጂነር አብደላ ከማልን ጨምሮ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ፣ የዩኒቨርሲቲው የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ኃ/ማርያም እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው ተመራማራዎች፣ ሴኔት አባላትና መምህራን እየተሳተፉ ይገኛሉ።

‎ዘጋቢ፡ አስናቀ ካንኮ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን