ለውጤታማ የጤና ተግባራት አፈፃፀም ለዘርፉ ባለሙያዎች ዕውቅና መስጠትና በአገልግሎት አሰጣጥ ለሚፈጠሩ ውስንነቶች ተጠያቂነትን በማስፈን የጤናውን ዘርፍ ብልፅግና ማሣደግ እንደሚገባ ተገለፀ

ለውጤታማ የጤና ተግባራት አፈፃፀም ለዘርፉ ባለሙያዎች ዕውቅና መስጠትና በአገልግሎት አሰጣጥ ለሚፈጠሩ ውስንነቶች ተጠያቂነትን በማስፈን የጤናውን ዘርፍ ብልፅግና ማሣደግ እንደሚገባ ተገለፀ

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ዓመታዊ የጤና ጉባዔውን እያካሔደ ሲሆን በጉባዔው ላይ የ2017 በጀት ዓመት የጤና ሴክተር ዕቅድ አፈፃፀም በቢሮው የልማት ዕቅድና የኢኮኖሚ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አይሌ ለማ ለጉባዔው ተሣታፊዎች ቀርቧል።

በሪፖርቱ እንደተመላከተው ከሆነ፤ የጤናውን ዘርፍ አገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና ተደራሽነት ለማሳደግ የጤና ኤክስቴንሽ ፕሮግራምን በማነቃቃት በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ውጤት መምጣቱም ተጠቁሟል።

በቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት፣ በቅድመ ወሊድ አገልግሎት፣ ነፍሰ ጡር እና ወላድ እናቶች ማቆያ አዘጋጅቶ አገልግሎት በመስጠት እንዲሁም በሌሎች ተግባራት በ2017 የተሻለ እና እያደገ የመጣ አፈፃፀም የተመዘገበ ሲሆን በተለይ በሰለጠኑ የማዋለድ ባለሙያዎች ለነፍሰ ጡር እናቶች የሚሰጠው አገልግሎት በቀጣይ በላቀ ደረጃ መሻሻል እንደሚገባው ነው በሪፖርቱ የተመላከተው።

የጤናና ጤና ነክ ድንገተኛ አደጋዎችን በመከላከል ረገድ የጎርፍ አደጋ፣ የወባ፣ የኩፍኝና የኮሌራ ወረርሽኞችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተደረገው ያላሰለሰ ጥረት በክልሉ አጥጋቢ ውጤት የተገኘበት እንደነበረ ሪፖርቱ አመላክቷል።

የጤና ስርዓት ቁጥጥርን በተመለከተ በጤና ተቋማት ቁጥጥር እና እድሳት የሚታይ ለውጥ የመጣ ቢሆንም በቀጣይ በላቀ ትኩረት ሊሠራበት ይገባል ተብሏል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሣሙኤል ዳርጌ ሪፖርቱን መነሻ በማድረግ የተደረገውን የውይይት መድረክ የመሩ ሲሆን በሪፖርቱ በቀረቡ ውስንነቶች ላይ በጥልቀት ተነጋግሮ ችግሮቹን በ2018 በጀት ዓመት መፍታት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ጉባዔው በሁለተኛ ቀኑ የ2017 በጀት ዓመት አፈፃፀም እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ቀርቦ ውይይት ከተደረገ በኋላ ለ2018 በጀት ዓመት ከሁሉም መዋቅሮች ጋር የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈርሞ ርክክብ የሚደረግ ይሆናል፡፡

በመጨረሻም በ2017 በጀት ዓመት ከፍተኛ አፈፃፀም ላስመዘገቡ መዋቅሮች እና ተቋማት ለተሻለ አፈጻፀም የሚያነሳሳ ሽልማትና ዕውቅና እንደሚሰጣቸው ለማወቅ ተችሏል።

ዘጋቢ፡ ወገኔ አየለ