ኢሬቻ አብሮነት፣ ወንድማማችነት እና ሕብረ ብሔራዊ አንድነት የሚጎላበት በዓል መሆኑን የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር ገለፁ

ኢሬቻ አብሮነት፣ ወንድማማችነት እና ሕብረ ብሔራዊ አንድነት የሚጎላበት በዓል መሆኑን የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር ገለፁ

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር እና ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት የኢሬቻ በዓልን ለማክበር የሚሄዱ የኦሮሞ ወንድምና እህቶችን ተቀብሎ የሽኝት መርሃግብር አካሂዷል፡፡

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር እንደገለፁት፤ ኢሬቻ ፆታና ሀይማኖት ሳይለይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለምስጋና፣ ለፍቅር፣ ለእርቅና ለይቅርታ የሚሰባሰብበት በዓል ነው።

የጉራጌ ህዝብ ከኦሮሞ ህዝብ ጋር የጠበቀ ግንኙነት አለው ያሉት አቶ ሙራድ የዛሬው የአቀባበል ፕሮግራም ለእሬቻ እና ለኦሮሞ ህዝብ ያለንን ክብር ለማሳየት ነው ብለዋል፡፡

በተለይ ደግሞ የዘንድሮውን ኢሬቻ በዓል ትልልቅ ሀገራዊ ስኬቶች ባሳካንበትና ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በተጠናቀቀበት ወቅት የሚከበር በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ነው ያሉት።

አቶ ሙራድ አክለውም የኢሬቻ በዓልን ከኦሮሞ ወገኖቻችን ጋር በጋራ ስናከብር ለጋራ ብልፅግና፣ ለአብሮነት እንዲሁም ወንድማማችነትን ይበልጥ በሚያጎለብት መልኩ መሆኑንም አንስተዋል።

ያሲን አባቡልጉና ኮ/ል ሪጃሉ ኡመር የጅማ ከተማ አባገዳዎች ናቸው፡፡ ኢሬቻ ፆታ፤ ሀይማኖት እንዲሁም ዘር ሳይለይ የሚከብር በዓል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የጉራጌ ህዝብ ከኦሮሞ ህዝብ ጋር በጋብቻና በደም የተዛመደ ህዝብ ነው ያሉት አባገዳዎቹ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ላደረገላቸው አቀባበል አመስግነዋል።

መሳይ ደሬሳና ናስር አባፊጣ የአባገዳ አባላት ሲሆኑ ኢሬቻ በአል ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን የምናጠናክርበት በዓል መሆኑን በማንሳት የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ባደረገላቸው አቀባበል መደሰታቸውን ገልፀዋል።

ዘጋቢ፡ አስፍር ሙህዲን – ከወልቂጤ ጣቢያችን