የተለያዩ የውሃ አጠቃቀም ዘዴዎችን ተግባራዊ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ አሳሰበ

የተለያዩ የውሃ አጠቃቀም ዘዴዎችን ተግባራዊ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ አሳሰበ

የቢሮው በ2017 ዓመተ ምህረት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትና የመደበኛ መስኖ አፈጻጸም ግምገማና የ2018 ዕቅድ ንቅናቄ መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ከንቅናቄው በኋላ በፍጥነት ወደስራ በመግባት የሚስተዋለውን አመቺ የአየር ሁኔታ መጠቀም ይገባል ብለዋል።

የውሃ አማራጭን ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችሉ የእርሻ መሣሪያዎችን ዝግጁ ማድረግና ጥገና የሚያስፈልጋቸውን የመስኖ አውታሮች በመጠገን በሙሉ አቅም መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

በክልሉ በአጠቃላይ ከ4 ሺ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት የሚያስችሉ 93 የመስኖ አውታሮች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህም 63 የመስኖ አውታሮች ከ2 ሺ ሄክታር በላይ ማሣ ማልማት በሚያስችል ደረጃ ላይ ይገኛሉ ነው ያሉት።

እነዚህን በአግባቡ በመጠቀም እንዲሁም የተለያዩ የውሃ አጠቃቀም ዘዴዎችን ተግባራዊ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

መመሪያን እና ህግን በተከተለ መንገድ የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ተቋማትን በማደራጀትና በማጠናከር በአግባቡ ወደስራ ማስገባት የትኩረት አቅጣጫ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

በንቅናቄ መድረኩ የበጋ መስኖ ስንዴና የሆርቲካልቸር ሰብሎች ልማት ያለፈው ዓመት አፈፃፀምና የዘንድሮ እቅድ ቀርበው ውይይት ተደርጓል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በመሰጡት አስተያየት ውይይቱ ለቀጣይ ስራ ውጤታማነት አጋዥ እንደሚሆን በመጠቆም ከክልል በታች በሚገኙ መዋቅሮች ለማስቀጠል እንደሚተጉ ተናግረዋል።

የውሃ አማራጮችን በአግባቡ በመጠቀም ካለፉት ጊዜያት በላቀ ውጤታማነት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ስራን ማሣካት በትብብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሻሻል መስራት እንደሚገባ በመስማማት የንቅናቄ መድረኩ ተጠናቋል።

በበጋ መስኖ ስንዴ እና በሆርቲካልቸር ልማት ዘርፎች ውጤታማ ለሆኑ አካላትም እውቅና ተሰጥቷል።

ዘጋቢ፡ ዮሐንስ ክፍሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን