ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት በየአካባቢው የሚደረጉ የእግር ኳስ ውድድሮች ወሳኝ እንደሆኑ ተገለፀ
”ስፖርት ለጤንነት እና ለሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል በይርጋጨፌ ከተማ ሲካሄድ የሰነበተው የእግር ኳስ ሻምፒዮና ማጠቃለያውን አግኝቷል።
በማጠቃለያው የተገኙት የጌዴኦ ዞን ወጣቶችና ሰፖርት ምክትል ሀላፊ እና የስፖርት ዘርፍ ሃላፊ ወ/ሮ ምስጋና በቀለ፤ በየአካባቢው የሚካሄዱ ስፖርታዊ ውድድሮች ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ያላቸው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ገልፀዋል።
በይርጋጨፌ ከተማ በእግር ኳስ ስፖርት እምቅ አቅም ያላቸው በርካታ ስፖርተኞች ያሉ በመሆኑ በትኩረት ከተሰራ ከአካባቢው አልፈው ሀገርን ሊወክሉ የሚችሉ ወጣቶች የታዩበት ውድድር በመሆኑ ቀጣይ ትኩረት ሰጥተን በዕቅድ እንሰራለን ያሉት ደግሞ የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ታደለ ጥላሁን ናቸው።
የይርጋጨፌ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ባህሩ ማሞ በበኩላቸው፤ ለአንድ ሳምንት ያክል ሲካሄድ የሰነበተው የእግር ኳስ ሻምፕዮና ጥሩ ስነ-ምግባርና ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች የታዩበት እንደነበር ተናግረዋል።
ከማዘውተሪያ ስፍራ ጋር ተያይዞ ችግሮች እንዳሉ ያነሱት ሀላፊው፤ ለቀጣይ ዞኑ እቅድ ስለያዘ በቅርብ ጊዜ ይስተካከላል ብለዋል።
የክረምት ወራት በጎ ፈቃድ ማጠቃለያ አካል የሆነው የእግር ኳስ ጨዋታ በከተማው በሚገኙ አምስት ቀጠናዎች መካከል ለአንድ ሳምንት ሲካሄድ ቆይቶ “ደንቢ እግር ኳስ ቡድን” “ዶንቦስኮ እግር ኳስ ቡድን”ን 2 ለ 1 በማሸነፍ የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል።
በውድድሩ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የእውቅና እና የምስክር ወረቀት ተሰጥቶ ማጠቃለያውን አግኝቷል።
ዘጋቢ: ወርቅአገኘሁ ወልደየስ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት በየአካባቢው የሚደረጉ የእግር ኳስ ውድድሮች ወሳኝ እንደሆኑ ተገለፀ

More Stories
የፕሪሚዬር ሊጉ የመክፈቻ ሳምንታት ጨዋታዎች በሀዋሳ እንደሚካሄዱ ተገለፀ
ብሩኖ ፈርናንዴዝ ወደ ሳውዲ ፕሮ ሊግ የማቅናት ፍላጎት እንደሌለው ተገለፀ
የሰርከስ ስፖርት ሳይንሳዊ ጥበቡን ጠብቆ ለማጎልበት በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ