በጋሞ ዞን ውስጥ ያሉ የሶስቱን ነባር ብሔረሰቦች ዘመን መለወጫ በዓላቸውን ጨምሮ ቋንቋን፣ ታሪክንና ባህላዊ ዕሴቶችን በጥናትና ምርምር በማጉላት ለተጠቃሚነት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ተገለፀ

በጋሞ ዞን ውስጥ ያሉ የሶስቱን ነባር ብሔረሰቦች ዘመን መለወጫ በዓላቸውን ጨምሮ ቋንቋን፣ ታሪክንና ባህላዊ ዕሴቶችን በጥናትና ምርምር በማጉላት ለተጠቃሚነት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ተገለፀ

‎‎የጊዲቾ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ “ባላ ካዳቤ ዮዮዮ” በዓል በተለያዩ ባህላዊ ሥርዓቶች በድምቀት እየተከበረ ይገኛል ።

‎‎የጋሞ ዞን መንግስት ዋና ተጠሪ እና የዕለቱ የክብር ዕንግዳ አቶ ሀኪሜ አየለ  ከሶስቱ ብሔረሰቦች  አንዱ የሆነው የጊዲቾ  ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ “ባላ ካዳቤ” በዛሬው ዕለት ለዘላቂ ልማትና አንድነት  በጋራ የምናከብረው በዓል በመሆኑ የእንኳን አደረሳችሁ  መልዕክታቸውን  አስተላልፈዋል።

‎‎የዚህን በዓል አከባበርን ልዩ የሚያደርገው ከተስፋ ወደሚጨበጥ ብርሃን የተሸጋገርንበት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተመረቀበት ወቅት መሆኑ ነው ብለዋል።

‎‎የብርብር ከተማ አስተዳደር የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ ስትሆን በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሮ ሀብት እንዲሁም የመንፈሳዊ ቦታዎች የቱሪስት መስህብ ባለቤት መሆኗንም የብርብር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብሪሃም አይካ ተናግረዋል።

‎‎በብርብር ከተማ አስተዳዳር በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል ትልቁን ሥፍራ የሚይዘው በጊዲቾ  ብሔር ዘመን መለወጫ የ”ባላ ካዳቤ  ዮ” በዓል ነውም ብለዋል።

‎‎የጊዲቾ ብሔር የበርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቱፊቶች ባለቤት ከሆኑት በክልሉ ከሚገኙ ብሔረሰቦች አንዱ ሲሆን የዘመን መለወጫ በዓሉን “ባላ ካዳቤ” በማለት ይጠራል ነው ያሉት ፡፡

‎‎”ባላ ካዳቤ” በብሄሩ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ታላቅ በዓል ሲሆን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ የብሔሩ ማንነት መገለጫ የሆነው የአሮጌው ዓመት ማብቂያና የአዲሱ ዓመት የመሸጋገሪያ በዓል ነው፡፡

‎‎የጊድቾ ብሔረሰብ የራሱ የሆነ ቋንቋ ፣ ባህል፣ ታሪክ ፣ውብ  ትውፊት ያለው   ዘመን  የዘለቀ እጅግ የጠለቀ የቱባ ባህላዊ እሴቶች ባለቤት ነው  ።

‎‎”ባላ  ካዳቤ  ዮ” ለጊዲቾ ብሔረሰብ አዲስ ምዕራፍ አዲስ ተስፋ ጅማሮ፣ ዘመድ ከአዝማድ መገናኛና መጠያየቅያ ፣የመትረፍረፍ የፍቅር፣ የመተሳሰብ በዓል መሆኑን ከንቲባው  ገልጸዋል ።

‎‎”ባላ ካዳቤ ዮ” በዓል ለቱሪዝም ሀብት እንዲውል የማልማትና የማስተዋወቅ  ሥራን ከተማ አስተዳደሩ በትኩረት እንደሚሠራ  ከንቲባው አረጋግጠዋል።

‎‎በበዓሉ አከባበር የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልና የጋሞ ዞን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የምዕራብ ዓባያ እና የብርብር ከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች ፣ የኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ጉጂ ዞን ዕንግዶች ፣ የጊዲቾ ብሔረሰብ ምሁራን የሀገር ሽማግሌዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው ዕንግዶች እና የብሔረሰቡ አባላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

‎‎ዘጋቢ፡- ሰለሞን አላ ከአርባምንጭ ጣቢያችን