በኧሌ ዞን ኮላንጎ ከተማ ከ165 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የኮላንጎ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሄደ

በኧሌ ዞን ኮላንጎ ከተማ ከ165 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የኮላንጎ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታ ማስጀመሪያ መርሐ ግብርም ተካሄደ

ሀዋሳ፣ መስከረም 08/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በኧሌ ዞን ኮላንጎ ከተማ ከ165 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የኮላንጎ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታ ማስጀመሪያ መርሐ ግብርም ተካሄዷል፡፡

የሆስፒታሉ ግንባታ ሕብረተሰቡ በጤናው ዘርፍ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ሊፈታ የሚችል መሆኑን የደቡብ  ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቋል።

በደቡብ  ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ተወካይ እና የጤና ልማት  እቅድና ኢኮኖሚ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር  አቶ ተገኝ ጮቴ እንደገለፁት ቢሮው የክልሉን የጤና ሽፋንና የአገልግሎት ተደራሽነት በማሳደግ የእናቶችና የሕፃናትን ሞት ለመታደግ እየሠራ መሆኑን ተናግረው የዚሁ አካል የሆነው የኮላንጎ  የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታን ናታሊያ ከተሰኘ የግንባታ ተቋራጭ ጋር ከ165 ሚሊዬን 345 ሺህ ብር በላይ  በሆነ ወጪ  ውል በመግባት ሥራ ማስጀመሩን አስረድተዋል።

የኧሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አርሻሌ አርካሌ እና የዞኑ ጤና ዪኒት አስተባባሪ  አቶ  ዘመኑ ዘንዳኦ በጋራ እንደገለፁት የኮላንጎ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታ መጀመሩ በጤናው ዘርፍ  የማህበረሰቡን የቆየ የመልካም አስተዳደር  ችግርን  እንደሚቀርፍ ገልፀው  በግንባታው ሂደት አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል ይደረጋል ብለዋል።

የናታሊያ ግንባታ ተቋራጭ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድማገኝ በቀለ በበኩላቸው በማህበረሰቡ ስለተደረገው አቀባበል አመስግነው ግንባታውን በጥራትና በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቃ ሁለንተናዊ ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

በአቅራቢያቸው  ሆስፒታል ባለመኖሩ የተሻለ ሕክምና ለማግኘት  ረጅም መንገድ ተጉዘው ለአላስፈላጊ ወጪ እና እንግልት ይዳረጉ እንደነበር አስታውሰው መንግስት ይህንን ችግር ለመቅረፍ የሆስፒታል  ግንባታ በማስጀመሩ መደሰታቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል ።

ዘጋቢ፡- ተመስገን አሰፋ ከጂንካ ጣቢያችን