በፍትህ ተቋማት ግልፀኝነትና ተጠያቂነትን ማስፈን ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ተባለ

በፍትህ ተቋማት ግልፀኝነትና ተጠያቂነትን ማስፈን ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ተባለ

ሀዋሳ፣ መስከረም 08/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በኮሬ ዞን ፍ/ቤቶችና የፍትህ ተቋማት ሪፎርም ፍኖተ ካርታ አፈጻጸም መመሪያ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ ተካሂዷል ።

የኮሬ ዞን ሽግግር ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ አካላት በቀለ፤ በፍትህ ስርዓቱ ተፈፃሚነት ላይ የፍ/ቤቶች ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ኃላፊነታቸውን በሚገባ መወጣት አለባቸው ብለዋል።

ከጀመረ ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረው የፍኖተ ካርታው ሪፎርም በየጊዜዉ በስትሪንግ ኮሚቴ እየተገመገመ መቆየቱን ጠቁመው የተጀመረውን ሪፎርም የማጥራት ተግባራትን ለማከናወን መድረኩ እንዳስፈለገ ነው የገለፁት ።

የኮሬ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አስታረቀኝ አንዳባ መንግስት በፍትህ ተቋማት ላይ የሚስተዋሉትን ክፍተቶች ለመሙላት ሪፎርም ቀርጾ በመስራት ላይ ይገኛል ነው ያሉት ።

በፍትህ ተቋማት የዳኝነት ግልፀኝነትና ተጠያያቅነት ማስፈን ፣ በሰብዓዊ መብት አያያዝ ማስተካከልና አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ከሁሉም ባለድርሻዎች ይጠበቃል ብለዋል።

በምክክር መድኩ ላይ የፍ/ቤቶችና የፍትህ ተቋማትን አፈጻጸም ለተሳታፊዎች ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል ።

በፍትህ ዘርፉ የተገልጋይ እርካታ ፣ የፍትህ ተደራሽነት፣ ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓትን ማጠናከር፣ ወንጀልን መከላከል ትኩረት ተሰጥቶባቸው ከተከናወኑ ተግባራት መካከል ተጠቃሾች እንደሆኑ በቀረበው ሰነድ ላይ ተመላክቷል።

የመድረኩ ተሳታፊዎችም ሪፎረሙ ከተጀመረ ወዲህ በፍትህ ተቋማት ላይ ለውጦች በመታየት ላይ እንዳሉ ጠቁመው በቀጣይ ለፍትህ ዘርፉ እንቅፋት የሚሆኑትን  በማጥራት  ሁላችንም የድርሻችንን መወጣት አለብን ሲሉ ተናግረዋል ።

ዘጋቢ : ለምለም ኦርሳ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን