ለመንግስት ሰራተኛው የተደረገውን የደመወዝ ማሻሻያ ምክንያት በማድረግ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር የተጠናከረ ክትትል እያደረገ መሆኑን የምስራቅ ጉራጌ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ

ለመንግስት ሰራተኛው የተደረገውን የደመወዝ ማሻሻያ ምክንያት በማድረግ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር የተጠናከረ ክትትል እያደረገ መሆኑን የምስራቅ ጉራጌ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ

መንግስት ነጋዴው ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርግ የሚያደርገው ክትትል ውጤት እያመጣ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ሸማቾች ገልጸዋል።

የምስራቅ ጉራጌ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ቤተልሄም ታደሰ ከደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ወልቂጤ ጣቢያችን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፤ በዞኑ የሸማቹና የንግዱን ማህበረሰብ መብት የጠበቀ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲኖር በትኩረት እየተሰራ ነው።

በተለይም ለመንግስት ሰራተኛው የተደረገውን የደመወዝ ማሻሻያ ምክንያት በማድረግ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ በየደረጃው ያሉ አስተዳደራዊ እርምጃዎችን በመውሰዱ ላይ የተጠናከረ ክትትል በመደረጉ ውጤት ማስመዝገብ ስለመቻሉም ሃላፊዋ አስረድተዋል።

ከዞን ጀምሮ የተቋቋመው ግብረ ሃይል ጠንካራ ስራ በመስራቱ በዘርፉ ሊከሰት የነበረውን ጫና መቀነስ እንደተቻለ በማንሳት በዞኑ የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ እንቅስቃሴ ባደረጉ 137 የንግድ ድርጅቶች ላይ በዚሁ ግብረ ሃይል አማካኝነት አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።

በተጨማሪም ለሁለንተናዊ እንቅስቃሴ መሰረት የሆነውና ወደ ዞኑ የሚገባው ነዳጅ በተገቢው ወደ ተጠቃሚው እንዲደርስ በየጊዜው እንደሚፈተሽ በመግለጽ በተደረገው ክትትልም በህገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ 1 ሺህ 9 መቶ ሊትር ነዳጅ በቁጥጥር ስር በማዋል ለመንግስት ገቢ ተደርጓል ነው ያሉት ሀላፊዋ ወይዘሮ ቤተልሄም።

በዋናነት ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ለመከላከል በሚደረገው እንቅስቃሴ ማህበረሰቡ ጥቆማ በመስጠት ረገድ አጋዥ ነው፡፡ ስለሆነም ይህንኑ ማስቀጠል እንዳለበት በመጠቆም በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላትም ያላቸውን ቅንጅታዊ አስራር ይበልጥ አጠናክረው ማስቀጠል እንዳለባቸው ሃላፊዋ አስገንዝበዋል።

የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተስፋዬ አህመድ በበኩላቸው፤ መንግስት ያደረገውን የደመወዝ ማሻሻያ መነሻ በማድረግ በከተማ አስተዳደሩ ተገቢነት የሌለው የዋጋ ጭማሪ እንዳይደረግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም በየደረጃው ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የዋጋ ጥናት ተደርጎ በግልጽ እንዲለጠፍ በማድረግ ሸማቹም ይህን ተመልክቶ ግብይት እንዲፈጽም እየተደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።

በመሆኑም ሸማቹ አግባብነት የሌለው የዋጋ ጭማሪ ሲመለከት የሚያደርገውን ጥቆማ አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበትም አመላክተዋል።

በቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ሲገበያዩ አግኝተን ካነጋገርናቸው ሸማቾች መካከል በሰጡት አስተያየት መንግስት ለሰራተኞች ያደረገውን የደመወዝ ማሻሻያ ተከትሎ በተለይም በፍጆታ እቃዎች ላይ ነጋዴው ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርግ የሚያደርገው ክትትል ውጤት እያመጣ በመሆኑ በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የምርት አቅራቢ ነጋዴዎች በበኩላቸው በምርት አቅርቦቱ ላይ ከመንግስት ጋር ተቀናጅተው እየሰሩ ስለመሆኑ ገልጸው በዚህም በተቀመጠው የመሸጫ ተመን መሰረት እንደሚሸጡ ገልጸዋል።

በስመ ደመወዝ ማሻሻያ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ ተገቢ አለመሆኑንና ወገንንም መጉዳት በመሆኑ መሰል ተግባራት የሚፈጽሙ አካላት ትክክል ባለመሆናቸው መንግስት ክትትል በማድረግ እርምጃ መውሰዱን ማስቀጠል ይኖርበታል ነው ያሉት።

ዘጋቢ፡ አማን ቢካ – ከወልቂጤ ጣቢያችን