የጊዲቾ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ ”ባላ ካዳቤ ዮዮዮ” በዓል በተለያዩ ባህላዊ ሁነቶች ታጅቦ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል

የጊዲቾ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ ”ባላ ካዳቤ ዮዮዮ” በዓል በተለያዩ ባህላዊ ሁነቶች ታጅቦ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል

‎የጊዲቾ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ ”ባላ ካዳቤ ዮዮዮ” በዓል በጋሞ ዞን ብርብር ከተማ አስተዳደር አልጌ ቀበሌ በተለያዩ ባህላዊ ሁነቶች ታጅቦ በድምቀት እየተከበረ ነው።

‎የብርሃን በዓል የሆነው “ባላ ካዳቤ” ከጨለማው ወደ ብርሃን እንዲሁም ከክረምት ወደ በጋ መሸጋገሪያ የአብሮነትና የመተሳሰብ በዓል ነው።

‎የጊዲቾ ብሔረሰብ የበርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ትውፊቶች ባለቤት ከሆኑት በክልሉ ከሚገኙ ብሔረሰቦች አንዱ ሲሆን የዘመን መለወጫ በዓሉን “ባላ ካዳቤ” በማለት እንደሚጠሩት የብርብር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብርሃም አይካ ተናግረዋል፡፡

‎”ባላ ካዳቤ” በብሔሩ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው ታላቅ በዓል መሆኑን የጠቆሙት ከንቲባው፤ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ የብሔረሰቡ ማንነት መገለጫ፣ የአሮጌው ዓመት ማብቂያና የአዲሱ ዓመት የመሸጋገሪያ በዓል ነው ብለዋል፡፡

‎የዘንድሮውን “ባላ ካዳቤ” በዓል አከባበር ልዩ የሚያደርገው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተመርቆ ኢትዮጵያንና ትውልደ ኢትዮጵያን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ደስታቸውንና ምስጋናቸውን በሚያቀርቡበት ወቅት መሆኑ ነው።

‎የብርሃን፣ የአንድነት፣ የዕርቅ፣ የፍቅርና የሰላም ተምሳሌት የሆነው ”ባላ ካዳቤ’ ዮዮዮ’ በዓል ባህላዊ አስተዳደርን፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፀጋዎችን በውስጡ አቅፎ ያየዘ በብሔረሰቡ ዘንድ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው በዓል መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በብርብር ከተማ አስተዳደር የባህልና ቱሪዝም ሥራ ክፍል አስተባባሪ አቶ ደርጉ ለገሠ ናቸው።

‎ባላ ካዳቤ መድረሱን የሚያበስሩ በብሔረሰቡ ዘንድ ”ሶምቦሎልተ” ተብለው የሚጠሩ ወፎች ከምስራቅ ወደ ደቡብ በየረድፋቸው እየበረሩ የሚያልፉበት ወቅት በመሆኑ በአዋቂዎችና በወጣቶች በኩል የሚደረግ ቅድመ ዝግጅቶች ጊዜ ተሰጥቶት እንደሚከናወኑ የጊዲቾ ብሔረሰብ ሀገር ሽማግሌ አቶ ባላሞ ወርባ ተናግረዋል።

‎በሴቶች በኩል ከቅድመ ዝግጅቶች ጀምሮ የሚከናወኑ ተግባራት እንዳሉ ወ/ሮ ሰላማዊት ፋሩሲ እና ወ/ሮ አስቴር ሸርካ ተናግረዋል።

‎”ባላ ካዳቤ”ን ጨምሮ የብሔረሰቡን ቋንቋ፣ ታሪክና ባህላዊ ዕሴቶችን በመጠበቅ፣ በመንከባከብና በማልማት ለቀጣይ ትውልድ በማሸጋገር ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ትኩረት ሊሰጠው አንደሚገባ ከብሔሩ ተወላጅ ምሁራን መካከል አቶ ገቦ ዶጃሞ ገልጸዋል።


ዘጋቢ፡ ሰለሞን አላሶ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን