በጋራ ተባብረን የህዳሴ ግድብን እንዳሳካን የማህበረሰባችን የጤና ችግሮችን በተለይም እናቶችንና ህጻናትን በዘላቂነት ከወባ በሽታ መታደግ እንችላለን – ሚኒስትር ዴኤታ ደረጀ ዱጉማ (ዶ/ር)
በጋራ ተባብረን የህዳሴ ግድብን እንዳሳካን የማህበረሰባችን የጤና ችግሮችን በተለይም እናቶችንና ህጻናትን በዘላቂነት ከወባ በሽታ መታደግ እንችላለን ሲሉ የኢፌዴሪ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ደረጀ ዱጉማ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ከፍተኛ የወባ ስርጭት ባለባቸው ወረዳዎች ለህጻናት የሚሰጠው የወባ መከላከያ ክትባትና የመኝታ አጎበር ስርጭት ዘመቻ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ቤተሰባችንንና ራሳችንን ከወባ በሽታ እንጠብቅ፤ አጎበር እንጠቀም፤ ልጆቻችንን እናስከትብ በሚል መሪ ቃል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን በቱርሚ ከተማ ተካሂዷል።
በማስጀመሪያው መርሐ ግብሩ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ፤ በዞኑ በሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች በተደጋጋሚ የወባ በሽታ መከሰቱን ጠቁመው በ2017 በጀት አመት የወባ በሽታ ምርመራ ከተደረገላቸው 216 ሺህ 545 የማህበረሰብ ክፍሎች ውስጥ 90 ሺህ 542 ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን ተናግረዋል።
ዋና አስተዳዳሪው አቶ ማዕከል አክለውም፤ ዞኑ ከኬንያና ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚዋሰን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የዝንጀሮ ፈንጣጣ፣ የኢቦላና ሌሎችም በሽታዎች የመዛመት ዕድል ስለሚኖር የፌዴራል መንግሥት ለአካባቢው ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል።
የዞኑ ማህበረሰብ አርብቶ አደርና የተራራቀ የአሰፋፈር ስርዓት ስላለው የጤና አገልግሎቶችን በተሟላ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ የተሽከርካሪ እጥረት በመኖሩ በመንግሥትና በሌሎችም ድርጅቶች ድጋፍ እንዲደረግልን እንጠይቃለን ሲሉ አቶ ማዕከል አንስተዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ እና የጤና ፕሮግራሞች ዘርፍ ሀላፊ አቶ መና መኩሪያ በበኩላቸው፤ የወባ በሽታ በክልሉ በአብዛኛው አካባቢዎች በከፍተኛ ሁኔታ ጫና መፍጠሩን ገልፀው በህዝቡ ላይ የጤና ችግር ብቻ ሳይሆን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶችንም የሚያስከትል ነው ብለዋል።
ምክትል ቢሮ ኃላፊው አቶ መና ከ5 አመት በታች ያሉ ህጻናት ለወባ በሽታ ይበልጥ ተጋላጭ ከመሆናቸው አንጻር የወባ መከላከያ ክትባት መጀመሩ ለወባ መከላከልና መቆጣጠር ትግበራ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ሲሉ ተናግረዋል።
የአለም ጤና ድርጅት (WHO) RW ተወካይ ሰለይ ማሪዋ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የወባ በሽታ ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየሄደች ያለችው ሂደት የሚደነቅ ነው ያሉ ሲሆን፤ የወባ በሽታ የእናቶችንና ህጻናትን ህይወት እንዳይቀጥፍ የሁላችንንም ትኩረት ያስፈልጋል ብለዋል።
ሰለይ ማሪዋ (ዶ/ር) አክለውም፤ በአለማችን እ.አ.አ በ2023 ብቻ በወባ በሽታ ከ600 ሺህ ሰዎች በላይ በበሽታው ህይወታቸውን አጥተዋል ከዚህም ውስጥ 95 በመቶ የሚሆኑ ዜጎች በአፍሪካ የሚገኙ መሆኑን ጠቁመው በበሽታው ከሚጠቁ ማህበረሰብ ክፍሎች መካከል በአማካይ 430 ሺህ የሚጠጉት ዕድሜያቸው ከ5 አመት በታች መሆናቸው አሳሳቢ ያደርገዋል ብለዋል።
ኢፌዴሪ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስቴር ዴኤታ ደረጀ ዱጉማ (ዶ/ር) በመድረኩ ባደረጉት ንግግር፤ ወባ የጤና ችግር ብቻ ሳይሆን በአምራቹ ሀይል ላይ ጉዳት የሚያደርስ በሽታ በመሆኑ ህዳሴን በጋራ ተባብረን እንዳሳካን የማህበረሰባችን የጤና ችግሮችን ለመቅረፍ ሁሉም ማህበረሰብ የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
እናቶችና ህጻናት በሽታ የመከላከል አቅማቸው ዝቅተኛ ስለሆነ በቀላሉ ለሞትና ለተለያዩ በሽታዎች ተጋላጭ ናቸው ያሉት የጤና ሚኒስትር ዴኤታው፤ የወባ በሽታ በተወሰነ መልኩ የመቀነስ ሁኔታ ቢኖርም በተለያዩ ምክንያቶች ከባለፈው ሦስት አመታት ወዲህ በአንዳንድ አካባቢዎች የስርጭት መጠኑ መጨመሩን አንስተዋል።
የበሽታውን ስርጭት ለመግታትና ለመቆጣጠር ከ2017 ጀምሮ ከ12 ሚሊዮን በላይ አልጋ አጎበር በፌዴራል ጤና ሚኒስቴር ግዢ ተፈጽሞ ስርጭት ለማድረግ የታቀደ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 5.9 ሚሊዮን አጎበር በስርጭት ላይ እንደሆነና 7 ሚሊዮን ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ ይገኛል ተብሏል።
በዛሬው ዕለት በተጀመረው የወባ ክትባት ዘመቻ በደቡብ ኦሞ ዞን በሳላማጎ ወረዳና በቱርሚ ከተማ አስተዳደር ለ1 ሺህ 749 ህጻናት ተደራሽ የሚደረግ ሲሆን በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ በቱርሚ ከተማ የተጀመረው የወባ ክትባት ዘመቻ በ58 ወረዳዎች የሚካሄድ መሆኑም ተጠቁሟል።
ዘጋቢ: ጄታ ታገሠ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ አስተዳደር ሁለት ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቁ ዘመናዊ ሆቴሎችን ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ
በኧሌ ዞን ኮላንጎ ከተማ ከ165 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የኮላንጎ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታ ማስጀመሪያ መርሐ ግብርም ተካሄደ
በፍትህ ተቋማት ግልፀኝነትና ተጠያቂነትን ማስፈን ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ተባለ