የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስኬት ለወደባችን ጉዞ ትልቅ የሞራል ስንቅ ነው ሲሉ የጂንካ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስኬት ለወደባችን ጉዞ ትልቅ የሞራል ስንቅ ነው ሲሉ የጂንካ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ

ነዋሪዎቹ “በህብረት ችለናል!” በሚል መሪ ቃል የግድቡን መጠናቀቅን አስመልክቶ ባካሄዴት የድጋፍ ሰልፍ ላይ የተለያዩ መልዕክቶች ተላልፈውበታል።

የትኛውንም ሀገራዊ ልማት በሕብረት እንጂ በተጠናጥል ተንቀሳቅሰን የሚጠበቀውን ውጤት ስለማናስመዝገብ ያለን አማራጭ መደመር ብቻ ነው ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ግድቡ በመጠናቀቁ ትልቅ ኩራትና ደስታ እንደተሰማቸው ገልፀው በቀጣይ ፊታችንን ወደ ወደባችን እናዞራለን ብለዋል፤ ይህም በህብረት እንደሚሳካ ምንም ጥርጥር የለንም ሲሉ ቁጭታቸውን ገልፀዋል።

ለድጋፍ ሰልፈኞች መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ፀሐይ ወራሳ በትውልድ ቅብብሎሽ እና በለውጡ መንግስት በሳል አመራር ሰጪነት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ ወደ ተግባር በመግባቱ እንኳን ደስ አለን ብለዋል።

በግድቡ ግንባታ መላው ኢትዮጵያዊያን አሻራቸውን አሳርፈው ዛሬ ላይ ፍሬውን አይተው የሚደሰቱበት ጊዜ በመምጣቱ ትልቅ ስኬት ነው ሲሉም ሀላፊዋ ገልፀዋል።

በቀጣይ ወደብን ጨምሮ የተያዙ በርካታ የልማት ውጥኖችን በሕብረት አስጀምረን እናስጨርሳለን ደግሞም መሰል የድጋፍ ሰልፎችን እናካሂዳለን መላው ኢትዮጵያዊያን ለዚህ እጅ ለእጅ መያያዝ ይጠበቅብናል ብለዋል ወ/ር ፀሐይ።

የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ በሕብራዊ አንድነት ግድባችንን አጠናቀናል እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

ጀምረን የምንጨርስ እንጂ የምናቋርጠው ልማት የለም ያሉት አቶ አብርሃም ከተባበርንና ከተደመርን ተአምር መፍጠር እንችላለን ይህም በቀድሞ በአድዋ በአሁን ወቅት በታላቁ ህዳሴ ግድብ በተግባር ተረጋግጧል ።

በቀጣይ በሁሉም ልማቶች ላይ ዘምተን ድላችንን እናስቀጥላለን ሲሉም አቶ አብርሃም መልዕክት አስተላልፈዋል ።

በህዳሴ ግድብ የተገኘውን ልምድ በሌሎች ልማቶች ላይ እናስቀጥላለን ያሉት ደግሞ የጂንካ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሲሳይ ጋልሺ ናቸው።

በአንድነትና በሕብረት ኢትዮጵያዊያን እናበልጽጋለን ፣የኢትዮጵያ ብልጽግና አይቀረ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ለግድቡ ስኬት በሁሉም መስክ ድጋፍ ላደረጉ አካላትም ምስጋና ተችሯቸዋል ።

መርሐ ግብሩ በተለያየ ዝግጅት ደምቆ ተጠናቅቋል ።

ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን