የካፈቾ ዘመን መለወጫ “ማሽቃሮ” በቦንጋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ተከበረ

የካፈቾ ዘመን መለወጫ “ማሽቃሮ” በቦንጋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ተከበረ

የኮሌጁ ዲን ኢንስትራክተር አንዱዓለም ገብረመድህን ማሽቃሮ ከምክረቾ ስርዓት ጀምሮ ከማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ጋር ተያይዞ ሲከበር የቆየ ነው ብለዋል።

በዓሉ ከክረምት አዝመራ 77 ቀናት መጠናቀቅ ጋር ተያይዞ በወቅቱ በተደረጉ የግብርና እንቅስቃሴዎች የተመዘገቡ ወጤቶች ተገምግመው የተሻለ አፈጻጸም ያስመዘገቡ እውቅና የሚሰጣቸው እንዲሁም ድክመት ያሳዩ በጠንካሮች የሚተኩበት ስርዓት እንደነበር ተናግረዋል።

ይህ ስርዓት በአካባቢው የተሻለ ተግባር እንዲኖር የሚያበረታታ መሆኑን ጠቁመው፥ ይህንን ተሞክሮ ወደ ተቋማት እንዲሸጋገር ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በዓሉ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተጠናቀቀበትና የካፋ ነገስታት ዘውድና መቀመጫ ከረጅም ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደቀድሞ ቦታው በተመለሰበት ወቅት የሚከበር መሆኑ እጅግ የተለየ ያደርገዋል ብለዋል።

ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል አቶ ንጋቱ ዓለሙ፣ ኢንስትራክተር አስቻለው ገብረሚካኤል፣ አቶ ፍቃዱ ኃይሌ እና አቶ አስማማው ገዛኸኝ ማሽቃሮ የካፈቾ ብሔረሰብ የራሱ መገለጫ እንዳለው ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል።

በተለይም የካፋ የመጨረሻው ንጉስ ጋኪ ሻሮቺ ዘውድና መቀመጫቸው በተመለሰበት ወቅት በዓሉን በማክበራቸው መደሰታቸውን ጠቁመዋል።

በመጪዉ መስከረም 12 እና 13 ቀን 2018 ዓመተ-ምህረት በቦንጌ ሻምበቶ የሚከበረውን የብሔሩን ዘመን መለወጫ በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ አሰግድ ሣህሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን