ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሀገራዊ አንድነትና ኩራት ማሳያ ፕሮጀክት ከመሆኑም ባሻገር በመተባበርና በህብረት ለአንድ አላማ መቆም ከተቻለ የማይችል ነገር እንደሌለ የታየበት መሆኑን ተገለፀ
ሀዋሳ፡ መስከረም 08/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሀገራዊ አንድነትና ኩራት ማሳያ ፕሮጀክት ከመሆኑም ባሻገር በመተባበርና በህብረት ለአንድ አላማ መቆም ከተቻለ የማይችል ነገር እንደሌለ የታየበት መሆኑን የቀቤና ልዩ ወረዳ አስተዳደር ገለጸ፡፡
በቀቤና ልዩ ወረዳ “በህብረት ችለናል” በሚል መሪ ቃል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅን አስመልክቶ በወልቂጤ ከተማ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ እንደገለፁት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በራስ አቅም ችግሮችን የመፍታት አቅም ማሳደጊያ፣ ጀምሮ የመጨረስና ወደ ተሟላ የኢኮኖሚ ሉኣላዊነት የመሸጋገሪያ ፕሮጀክት ነው፡፡
የግድቡን ግንባታ በራሳችን ህዝብና በመንግስት አቅም አለምአቀፍ ጫናዎችን በመቋቋም ማጠናቀቅ በመቻላችን ለሀገሪቱ ፣ ለቀጠናውና ለአፍሪካ ትልቅ ብስራት ከመሆኑም በተጨማሪ የህዳሴ ማንቂያ ደወል ነው ሲሉ ተናግረዋል ፡፡
በቀጣይም እንደ ሀገርም ሆነ ክልል የታቀዱ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በመተባባር ማጠናቀቅና ስኬታማ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚገባ ገልፀዋል ፡፡
የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞሳ ኢዶሳ በበኩላቸው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በአንድነት በመቆምና አሻራቸውን በማኖር ለስኬት እንዲበቃ በማስቻል መጀመር ብቻ ሳይሆን መጨረስ እንደምንችል ያስመሰከርንበት ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል ፡፡
ለህዳሴው ግድብ ያሳየነውን ፅናትና አይበገሬነት በአካባቢያዊ ልማትና በሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ ማሳየት እንደሚገባም ገልፀዋል ፡፡
የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየትም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጠናቆ በመመረቁ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ “በህብረት ችለናል፣ የአንድነታችን መገለጫ ነው ፣ ግድቡ የእኔ ነው፣ የሚደገም ድል የሚጨበጥ ብስራት፣ የክብራችን ምንጭ ነው።” የሚሉና ሌሎችም መልዕክቶች ከተሳታፊዎች ተስተጋብተዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክልል ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ሙነቴ ሙንዲኖን ጨምሮ ሌሎችየክልሉና የልዩ ወረዳው አመራሮችና ባለሙያዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የልዩ ወረዳው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል ፡፡
ዘጋቢ፡ ወለላ ኤልያስ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
በጋራ ተባብረን የህዳሴ ግድብን እንዳሳካን የማህበረሰባችን የጤና ችግሮችን በተለይም እናቶችንና ህጻናትን በዘላቂነት ከወባ በሽታ መታደግ እንችላለን – ሚኒስትር ዴኤታ ደረጀ ዱጉማ (ዶ/ር)
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስኬት ለወደባችን ጉዞ ትልቅ የሞራል ስንቅ ነው ሲሉ የጂንካ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ
የካፈቾ ዘመን መለወጫ “ማሽቃሮ” በቦንጋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ተከበረ