የህዳሴው ግድብ የዳግም ነፃነት ፋና ወጊ፣ ራስን የመቻል አለኝታና የአይበገሬነት ምሳሌ መሆኑ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ መስከረም 08/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የህዳሴው ግድብ የዳግም ነፃነት ፋና ወጊ፣ ራስን የመቻል አለኝታና የአይበገሬነት ምሳሌ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መሀመድ ኑርዬ ገለፁ::
በጉራጌ ዞን “በህብረት ችለናል” በሚል መሪ ቃል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅን አስመልክቶ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በወልቂጤ ከተማ ተካሄዷል፡፡
በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መሀመድ ኑርዬ እንደገለጹት የህዳሴው ግድብ የዳግም ነፃነት ፋና ወጊ፣ ራስን የመቻል አለኝታና የአይበገሬነት ምሳሌ ነው::
ሀገሪቱ በምግብ ራስን ለመቻል ለምታደርገው ጉዞ ጠንካራ መሰረት እንደሆነ ገልፀው የዜጎችን የአኗኗር ዘይቤ ለማሻሻል ለሚደረገው እንቅስቃሴ አበርክቶው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል::
በመላው የሀገሪቱ ህዝቦች ድጋፍና ተሳትፎ የተገነባው ግድቡ የትብብርና የአንድነት ማሳያ መሆኑን ገልጸው፥ በተለይም በግንባታው ሂደት የነበሩትን ቀጣናዊና አለምአቀፋዊ ጫናዎች መቋቋምና ፈተናዎች የታለፉባቸው መንገዶች የዘመናት የአይበገሬነት ውጤት መሆኑን ዶክተር መሀመድ አስረድተዋል::
በቀጣይም የሀገሪቱ የልዕልናና የከፍታ ህልም እውን እንዲሆን አንድነት፣ አብሮነት፣ መደማመጥና መተባበር የሀገሪቱ ህዝቦች መርህ መሆን አለበት ብለዋል::
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበኩላቸው መተባበር፣ መደማመጥና በጋራ መቆም ከተቻለ የማይቻል ነገር እንደሌለ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል::
ግድቡ ዳግማዊ የአድዋ ድል ነው ያሉት አቶ ላጫ ኢትዮጵያውያን ለብሔራዊ ጥቅማቸው ሲሉ በጋራ የገነቡትና የኢትዮጵያ ተስፋና የዘመኑ ህያው መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል::
የኤሌክትሪክ ሀይል ተጠቃሚ ያልሆነውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ጠቁመው ይህም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማቱን እንደሚያሳድገው አስረድተዋል::
በግድቡ የተገኘውን ድል በሌሎችም ሀገራዊ፣ ክልላዊና ዞናዊ ፕሮጀክቶች ላይ መድገም እንደሚገባ አቶ ላጫ አስገንዝበዋል::
የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊዎች የሀገሪቱ ህዝቦች በሀሳብ፣ በገንዘብና በጉልበት በመተባበር ውጤት ያገኙበት በመሆኑ እድለኛ ትውልድ መሆናቸውን ተናግረዋል::
ግድቡ ለህብረ ብሔራዊ አንድነት መሰረት መሆኑን ገልፀው በአንድነትና በጋራ መስራት ከተቻለ የማይቻል ነገር እንደሌለ ማሳያ ነው ብለዋል::
የህዳሴው ግድብ የመቻል ማሳያ የማንሰራራት ጅማሮ ምልክት መሆኑን የገለፁት ነዋሪዎቹ የመነሳሳት ብስራት የኢትዮጵያዊነት ድምቀት ነው ብለዋል::
በህዳሴው ግድብ የተገኘውን ድል በሌሎችም ልማቶች ለመድገም ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል::
በህዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ ላይ የወልቂጤ ከተማ እና የአበሽጌ ወረዳ ነዋሪዎች፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ የመንግስት ሰራተኞች ፣ ተማሪዎች እና አርሶ አደሮች እንዲሁም የክልል፣ የዞኑና የከተማው ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ተሳትፈዋል::
ዘጋቢ: ሄኖክ ተክሌ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
በጎፋ ዞን 5ኛ ዩኒየን የሆነዉ የቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ዩኒየን መሰራች ኮሚቴ መድረክ በሳዉላ ከተማ ተካሄደ
የጊዲቾ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ ”ባላ ካዳቤ ዮዮዮ” በዓል በተለያዩ ባህላዊ ሁነቶች ታጅቦ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል
በጋራ ተባብረን የህዳሴ ግድብን እንዳሳካን የማህበረሰባችን የጤና ችግሮችን በተለይም እናቶችንና ህጻናትን በዘላቂነት ከወባ በሽታ መታደግ እንችላለን – ሚኒስትር ዴኤታ ደረጀ ዱጉማ (ዶ/ር)