የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከአገራችን አልፎ ለጎረቤት አገራት የብርሃን ምንጭ ከመሆን ባሻገር ቀጠናዊ ትስስርን የሚያጠናክር ነው ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ አበባዬሁ ታደሰ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የግድቡን መጠናቀቅ አስመልክቶ በአርባምንጭ ከተማ ከፍተኛ የሆነ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።
የአርባምንጭ ከተማ ከንቲባ መስፍን መንዛ(ዶ/ር) በድጋፍ ሰልፉ ላይ እንዳሉት፤ የዘመናት ቁጭት የሆነው የህዳሴው ግድብ በኛው ገንዘብ፣ እንባና ደም የታነፀና በከፍተኛ ህዝባዊ ገድል ተገንብቶ የተጠናቀቀ ነው።
በከተማው የሚገኙ አካላት ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ማሰባሰብ መቻሉንና በከተማው በማስተባበር ከፍተኛ ሚና ለተጫወቱት ምስጋና አቅርበዋል።
ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስም በሳል አመራር በመስጠት በብቃት መፈፀም እንደምንችል ያሳዩን ዶክተር ዐቢይ አሕመድን አድንቀው፤ በህዳሴው ያገኘውን ድል በሌሎች የልማት መስኮችም ለመድገም አንድነታችንን ከመቼውም ጊዜ በላይ በላቀ ሁኔታ ማሳየት ይኖርብናል ብለዋል።
የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምስ አድማሱ(ዶ/ር)፤ የህዳሴው ግድባችን በጠንካራ ወኔ የኢትዮጵያን ንጋት ያበሰረና ከፍታ ላይ ያወጣ ፕሮጀክት ነው። የለውጡ መንግስት ከመጣ ወዲህ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በሰጡት ጠንካራና በሳል አመራር ተጠናቆ መመረቁን አመላክተዋል።
ለጋራ አላማና ለአገራዊ አንድነት ከፍተኛ ስሜት ያለው የጋሞ ዞንም ከፍተኛ አበርክቶ እንደነበረው ጠቁመው፤ በቀጣይም የባህር በራችንን ለማስመለስ በሚደረገው ጥረትም ህብረተሰቡ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ አበባዬሁ ታደሰ (ዶ/ር) የጋራ ህልማችንን በጋራ ያሳካንበትን የህዳሴው ግድብ አንገታችንን ቀና ያደረገ፣ የላብና የደም መስዋዕት የተከፈለበት የአብሮነታችን መገለጫ ነው።
ግድቡ ከኛም አልፎ ቀጠናዊ ትስስርን የሚፈጥር ከመሆኑም ባሻገር ለኢትዮጵያውያን እና ለአፍሪካውያን የነፃነት አርማ በመሆኑ ለሀገር ብልፅግና ቁልፍ ሚና ይጫወታል ሲሉም ጠቁመዋል።
የጋራ ስኬት፣ የአብሮነት ተምሳሌትና የመንግስታችን ብስለት ያሳየንበት ፕሮጀክት ነው ያሉት ዶ/ር አበባዬሁ፤ የክልሉ ህዝብ ግድቡ በድል እንዲጠናቀቅ ሁለንተናዊ ድጋፍ ስላደረገም አመስግነዋል።
በቀጣይም በግድቡ የተገኙ ድሎችን በሌሎች የልማት መስኮችና የባህር በር መድገም አለብን ብለዋል።
የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊዎች የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመተባበር አቅማችንን ያሳየንበት የአባይን የጥንት ስም ታሪክ ያደረግነበት የጀግንነትና የድል አርማችን ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በህዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ ላይ የፈረስ ጉግስ፣ ወታደራዊ የሰልፍ ትርኢትና የስነ ጽሁፍ ስራዎች የቀረቡ ሲሆን የክልል፣ የዞን፣ የአርባምንጭ ከተማና የዙሪያ ወረዳ ከፍተኛ አመራሮችና የመንግስት ሰራተኞች እንዲሁም የከተማዋ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ፡ ማርታ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
More Stories
በጋራ ተባብረን የህዳሴ ግድብን እንዳሳካን የማህበረሰባችን የጤና ችግሮችን በተለይም እናቶችንና ህጻናትን በዘላቂነት ከወባ በሽታ መታደግ እንችላለን – ሚኒስትር ዴኤታ ደረጀ ዱጉማ (ዶ/ር)
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስኬት ለወደባችን ጉዞ ትልቅ የሞራል ስንቅ ነው ሲሉ የጂንካ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ
የካፈቾ ዘመን መለወጫ “ማሽቃሮ” በቦንጋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ተከበረ