ሀዋሳ፡ መስከረም 07/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በህዳሴ ግድብ ግንባታ የታየው አንድነት እና ትብብር በልማቱ እና በሰላሙ ላይ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በምክትል ርእሰ መስተዳደር ማእረግ የመሰረት ልማት ክላስተር አስባባሪ እና የመንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋጂኦ ሳፒ ገለጹ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቁን ተከትሎ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በቤንች ሸኮ ዞን በሚዛን አማን ከተማ ተካሂዷል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ እንደ ሌሎች የሀገሪቱ ህዝብ ሁሉ በቤንች ሸኮ ዞን የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ለህዳሴ ግድቡ ግንባታ ድጋፋቸውን በተለያየ መልኩ ሲገልጹ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
ከህጻን እስከ አዋቂ፣ ከመንግስት ሰራተኛው እስከ አርሶአደር፣ ከነጋዴ እስከ ሀይማኖት ተቋማት፣ ከሴቶች እስከ ወጣት አደረጃጀቶች፣ የጸጥታ አካላት ለግድቡ ቦንድ በመግዛት አሻራቸውን አኑረዋል።
ግድብ ተጠናቆ ለምረቃ በመብቃቱ ደስታቸውን የገለጹት የቤንች ሸኮ ዞን ነዋሪዎች በሚዛን አማን ከተማ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ ስሜታቸውን ያንጸባረቁ ሲሆን፥ የግድቡ ግንባታ እስከሚጠናቀቅም ቦንድ በመግዛት የድርሻቸውን ሲወጡ እና አሻራቸውን ሲያሳርፉ መቆየታቸውን ጠቁመዋል።
የግድቡ መጠናቀቅ የህዝቦችን የይቻላል መንፈስ ይበልጥ ያሳየ፣ የኢትዮጵያውያንን አንድነት ለአለም ያስመሰከረ፣ ጠላቶቻችንን አንገት ያስደፋ ኢትዮጵያዉያንን ቀና ያደረገ ትልቅ የሀገር ኩራት ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፥ ይህ የዘመኑ ሁለተኛው አደዋ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የታየው አንድነት በቀጣይ የአሰብ ወደብ ለማግኘት በሚደረገው ጥረት ላይ ሊደገም እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የሚዛን አማን ከተማ ከንቲባ አቶ ሰለሞን ሌዊ በበኩላቸው፥ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን የጋራ ጥረት፣ እውቀት፣ ጉልበት፣ ገነዘብ በመገንባቱ የነጻነት ኩራት፣ የአይበገሬነት እና የስኬት ተምሳሌት የጋራ ታሪካችን ሆኖ ቆሟል ብለዋል።
በህዳሴ ግድባችን ያሳየነውን አንደነት በከተማችን የልማት ተግባራት ላይ ተሳታፊ በመሆን የከተማዋን እድገት ማስቀጠልም ይገባል ብለዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍቲን በበኩላቸው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመላው ኢትዮጵያውያን ህዝብ አሻራ ያረፈበት የጽናት እና የትጋት ውጤት መሆኑን ጠቁመው፥ ግድቡ በርካታ ፈተናዎችን ተሻግሮ ለምረቃ መብቃቱም በመንግስት የተወሰደው ቁርጠኛ አመራር ውጤት እንደሆነም ተናግረዋል።
የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በምክትል ርእሰ መስተዳደር ማእረግ የመሰረት ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የመንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋጂኦ ሳፒ በበኩላቸው የታላቁ ህዳሴ ግድብ በርካታ ፈተናዎችን አልፎ ለምረቃ መብቃቱ እጅ ለእጅ ከተያያዝን የማንሻገረው ፈተና እንደሌለ ያሳየ መሆኑን ገልጸው፥ ለዚሁም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ሊመሰገኑ ይገባቸዋል ብለዋል።
እንደ ህዳሴ ግድቡ ሁሉ በርካታ ፋብሪካዎችን በየአከባቢያችን መገንባት ያስፈልጋል ያሉት አቶ ፋጂኦ በግድቡ ያሳየነው አንድነትን በአከባቢ ልማት እና ሰላም ሊደገም ይገባልም ብለዋል።
ግድቡ እውን እንዲሆን ዋጋ የከፈሉ የህብረተሰብ ክፍሎች አመሰግነዋል።
በድጋፍ ሰልፉ የተለያዩ ባህላዊ ጭፈራዎች እና የጸጥታ አካላት የሰልፍ ትርኢትም ደምቆ ተከብሯል።
ዘጋቢ፡ አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
በኢፌዴሪ የጤና ሚኒስትር ሚኒስቴር ዴኤታ ደረጄ ዱጉማ (ዶ/ር) የተመራ ልዑክ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በኣሪና ደቡብ ኦሞ ዞኖች የሥራ ጉብኝት አደረጉ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቡርጂ ዞን “በህብረት ችለናል” በሚል መሪ ቃል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በድል ተጠናቆ መመረቁን አስመልክቶ ዞናዊ የፓናል ዉይይት መድረክ ተካሄደ
አባይ ለጎረቤት አገራት መብራትና ድንበር ተሻጋሪ የዝምድና ገመድ ሆኗል – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ ዳርጌ ዳሼ