አባይ ለጎረቤት አገራት መብራትና ድንበር ተሻጋሪ የዝምድና ገመድ ሆኗል – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ ዳርጌ ዳሼ

‎ሀዋሳ፡ መስከረም 07/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) አባይ ለጎረቤት አገራት መብራትና ድንበር ተሻጋሪ የዝምድና ገመድ ሆኗል ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ ዳርጌ ዳሼ ገለጹ፡፡

“በህብረት ችለናል ! ጨርሰን አሳይተናል!” በሚል መሪ-ቃል ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን ተከትሎ በኮንሶ ዞን ካራት ከተማ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።

በድጋፍ ሰልፉ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የካራት ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ያቤሎ ኩሴ፥ የካራት ከተማ አስተዳደር ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያስፈልገውን የገንዘብ ድጋፍ ህብረተሰቡን በማስተባበር የድርሻቸውን ሲወጡ መቆየታቸውን አስታውቀዋል።

በተባበረ ክንድ ግድቡን ለፍጻሜ እንዳበቃን ሁሉ በአንድነት መንፈስ የአካባቢያችንን የልማት ፕሮጀክቶች ለፍጻሜ በማብቃት ብልጽግናችንን እናረጋግጣለን ብለዋል።

‎የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገሌቦ ጎልቶሞ በኢትዮጵያውያን አንድነትና ትብብር ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በድል ተጠናቅቆ ሁለተኛውን አድዋ እንዳስመዘገብነው ሁሉ አባይን ባሳኩ ክንዶች የባህር በራችንን ለማሳካት የሚያግደን ምድራዊ ኃይል አይኖርም ሲሉ ገልጸዋል ።

‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብሔረሰቦች ምክር-ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ ዳርጌ ዳሼ በበኩላቸው ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በራሳችን ሕዝብ ፣ በራስ ምህድስና ፣በራሳችን እውቀት እንዲሁም በራሳችን ሀብት መገንባት ችለናል ብለዋል።

ከግብፅ የበላይነት መንጭቀን አውጥተን ለሀገራችን የዓሣ መናኸሪያ የሥራ አጥ ዜጎች ሥራ ዕድል መፍጠሪያ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ሚዛን ጠባቂ፣ ለሚሊዮን ሕዝባችን መብራት በመስጠት ለሀገር ውስጥ ባለውለታ እንዲሆን አድርገናል።

‎አባይ ቤተሰባችንና ዘመዳችን አልፎ ማደጊያችን እንድሁም የፖለቲካ አጀንዳችን የኢኮኖሚ መሠረታችን ብሎም የውጭ ምንዛሪያችን ሆኗል እንኳን ደስ አለን አላችሁ ብለዋል ።

‎አስተያየት የሰጡን የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊዎች ግድቡን በህብረት እንዳሳከነው ሁሉ ሌሎችንም ፕሮጀከቶች ተባብረን እናሳካለን ሲሉ ተናግረዋል ።

‎ዘጋቢ፡ አዕላፍ አዳሙ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን