ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የህብረ ብሄራዊነታችንና የአንድነታች መገለጫ ከመሆኑም በላይ በላብና ደም የተገኘ ውጤት መሆኑ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ መስከረም 07/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድባችን የህብረ ብሄራዊነታችንና አንድነታችን መገለጫ ከመሆኑም በላይ በላብና በደም የተገኘ ውጤት ነው ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ም/ል ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ማሄ ቦዳ ገለጹ፡፡
በከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት ገንብተን ዘመን ተሻጋሪ የትውልድ አሻራ በማኖራችን ለመላው ኢትዮጵውያን ምስጋና ይገባል ተብሏል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ “በህብረት ችለናል”በሚል መሪ ቃል በአርባምንጭ ከተማ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የአርባምንጭ ከተማ ከንቲባ መስፍን መንዛ (ዶ/ር) እንዳሉት የኢትዮጵያ ኩራት፣ የአንድነታችን ማሳያ፣ የወል ስኬታችን የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በከፍተኛ መስዋእትነት መጠናቀቁን አንስተዋል።
በአድዋ የተገኘውን ታላቅ ድል አባቶቻችን ለኛ እንዳስረከቡን ሁሉ እኛም ለመጭው ትውልድ የሚተርፍና ብርሀን የሚሆን የታላቁን የህዳሴ ግድብ ተክለን ማቆም መቻላችን ትልቅ ኩራት ነው ብለዋል።
ለግድቡ ግንባታ ዝቅተኛ ገቢ ካለው እስከ ታዳጊ ተማሪ ድረስ በከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት ገንብተን ይህን ዘመን ተሻጋሪ የትውልድ አሻራ በማኖራችን ለመላው ኢትዮጵውያን ምስጋና ይገባናል ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጽያ ክልል ም/ል ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ማሄ ቦዳ አባይ ለዘመናት አፈራችንን እየሸረሸረ ለሌሎች ሀገራት ሲሳይ ሲሆን ከቆየበት አሁን ማደርያውን አግኝቶ እጅ መስጠቱ በይቻላል መንፈስና ብርቱ ጥረት በመገንባቱ ነው ብለዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከሀይል ምንጭነት ባሻገር በራስ አቅም መስራትን፣ ጫና መቋቋምን ያስተማረን፣ ከአይችሉም መንፈስ ወደ ይቻላል እንድንሸጋገር ያደረገ ድላችን መሆኑን ጠቅሰዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የህብረ ብሄራዊነታችንና የአንድነታች መገለጫ ከመሆኑም በላይ በላብና ደም የተገኘ ውጤት ነው ፤ በቀጣይ መሠል ፕሮጀክቶችን ለመገንባት በር የሚከፍት እንደሆነም ተናግረዋል።
በፓናል ውይይቱ ላይ ከአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ከዞንና ከክልል ተቋማት የተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮች ፣ ባለሙያዎችና ምሁራን እየተሳተፉበት ይገኛሉ።
ዘጋቢ፡ ማርታ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
More Stories
ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መመረቁን ተከትሎ “በህብረት ችለናል” በሚል መሪ ቃል የፓናል ውይይት መድረክ በጂንካ ከተማ ተካሄደ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቁ ኢትዮጵያ ከተስፋ ወደ ሚደነቅ ብርሃን መሸጋገሯን የሚያሳይ የአንድነት መገለጫ አገራዊ ፕሮጀክት መሆኑ ተገለጸ
ታላቁ የህዳሴ ግድብ ተጠናቆ መመረቅን ምክንያት በማድረግ የይርጋጨፌ ወረዳ እና ከተማ አስተዳደር በጋራ በመሆን የድጋፍ ሰልፍ አካሄዱ