ሪያል ማድሪድ እና ቶትንሃም ተጋጣሚዎቻቸውን ሲያሸንፉ ዩቬንቱስ እና ዶርትሙንድ አቻ ተለያይተዋል
በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ሪያል ማድሪድ እና ቶትንሃም ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ ውድድሩን በድል ጀምረዋል።
በሜዳው ኦሎምፒክ ዴ ማርሴን ያስተናገደው ሪያል ማድሪድ ከመመራት ተነስቶ 2ለ1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።
ለሎስብላንኮዎቹ ሁለቱንም የማሸነፊያ ግቦች ክሊያን ምባፔ በፍፁም ቅጣት ከመረብ ሲያሳርፍ ቲሞቲ ዊሃ የፈረንሳዩን ክለብ ከሽንፈት ያልታደገችውን ግብ አስቆጥሯል።
በጨዋታው የሪያል ማድሪዱ ተከላካይ ዳኒ ካርቭሃል በ72ኛው ደቂቃ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።
ክሊያን ምባፔ ለሪያል ማድሪድ በ64 ጨዋታዎች 50ኛ ጎሉን ነው ያስቆጠረው።
ሪያል ማድሪድ በሻምፒዮንስሊጉ እንደ አውሮፓውያኑ ከ1992 ወዲህ 700 ጎሎችን በማስቆጠር ቀዳሚው ክለብ ሆኗል።
ከ2 ዓመታት በኋላ ወደ አውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር የተመለሰው ቶትንሃም ቪያሪያልን 1ለ0 አሸንፏል።
ለሰሜን ለንደኑ ክለብ ብቸኛዋን የማሸነፊያ ጎል ሉይዝ ጁኒዬር በራሱ መረብ ላይ አሳርፏል።
በሌላ በኩል ጁቬንትስ እና ቦሩሲያ ዶርትሙንድ በአሊያንዝ ስታዲየም ያከናወኑት ጨዋታ 4 አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
ለጀርመኑ ክለብ ግቦችን ካሪም አዴይሚ፣ ንሜቻ፣ ኩቶ እና ቤንሴባይኒ ማስቆጠር ችለዋል።
ለጁቬንቱስ ደግሞ ዱሳን ቭላሆቪች 2 ግቦችን ሲያስቆጥር ኬናን ይልዲዝ እና ኬሊ ቀሪ ግቦችን ከመረብ አሳርፈዋል።
እንዲሁም ከሜዳው ውጪ ቤኔፊካን የገጠመው ቃራባግ ከ2ለ0 መመራት ተነስቶ 3ለ2 አሸንፏል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ
More Stories
የሴቶች የ3 ሺ ሜትር መሰናክል ፍፃሜ በዛሬዉ ዕለት ይካሄዳል
አትሌት ፍሬወይኒ ሃይሉ በሜዳልያ ሰንጠረዥ ውስጥ መግባት አልቻለችም
የሴቶች 1500 ሜትር የፍፃሜ ውድድር ከሰዓታት በኋላ ይካሄዳል