የካፋ ዞን ጤና መምሪያ የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2018 ዕቅድ ዝግጅት ላይ ውይይት እያካሄደ ነው

የካፋ ዞን ጤና መምሪያ የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2018 ዕቅድ ዝግጅት ላይ ውይይት እያካሄደ ነው

ሀዋሳ፡ መስከረም 06/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የካፋ ዞን ጤና መምሪያ የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2018 ዕቅድ ዝግጅት ላይ ያተኮረ ውይይት በቦንጋ ከተማ ማካሔድ ጀምሯል፡፡

የመምሪያው ኃላፊ አቶ አክሊሉ አሰፋ በመክፈቻ ንግግራቸው ፤ ከሀገራዊ ለውጥ ወዲህ የጤና ፖሊሲ ላይ ማሻሻያ ተደርጎ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በዞኑ አራት አንደኛ ደረጃና አንድ አጠቃላይ ሆስፒታሎች፣ 50 ጤና ጣቢያዎች፣ 292 መሰረታዊ ጤና ኬላዎች እና ሁለት ልዩ ጤና ኬላዎች እንደሚገኙ ጠቁመው፥ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ምርመራ ከተደረገላቸው 63 ሺህ 225 ሰዎች መካከል 202 አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ተገኝተው ህክምና እያገኙ ነው ብለዋል።

307 ሺህ በላይ ሰዎች በወባ በሽታ ተይዘው ህክምና እንዲያገኙ መደረጉን አቶ አክሊሉ አንስተዋል።

የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትን 78 በመቶ ማድረስ መቻሉን እና 54 ነጥብ 2 በመቶ የሚሆኑ እናቶች በጤና ተቋማት መውለዳቸውን የገለጹት ኃላፊው፥ ይህም የመረጃ አያያዝ ችግሮች እና በቤት ውስጥ የሚወልዱ እናቶች መኖራቸውን የሚያመላክት በመሆኑ ቀጣይ ትኩረት ይሰጣል ብለዋል።

የካፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ደመላሽ ንጉሴ በሽታን መከላከልና አክሞ የማዳን ስራ በተጠናከረ መልኩ መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል።

የመድሐኒት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ይሰራል ያሉት አቶ ደመላሽ ፤ ባለድርሻ አካላት በጀት አመዳደብ ላይ ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በመድረኩ የካፋ ዞን፣ የሁሉም ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች አመራሮች፣ የጤና ዘርፍ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው።

ዘጋቢ፡ ሀብታሙ ታደሰ – ከቦንጋ ጣቢያችን