መረጃ የሀገር ሀብት በመሆኑ ትክክለኛ መረጃ በመስጠት ሀገራዊ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል – የኢትዮጵያ ስታስቲክ አገልግሎት
ሀዋሳ፡ መስከረም 05/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) መረጃ የሀገር ሀብት በመሆኑ ትክክለኛ መረጃ በመስጠት ሀገራዊ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ሲል የኢትዮጵያ ስታስቲክ አገልግሎት አርባ ምንጭ ቅርንጫፍ አስታወቀ፡፡
የኢኮኖሚ ድርጅቶች ናሙና ቆጠራ አስመልክቶ ከ1ሺ በላይ ለሚሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች በአርባ ምንጭ ከተማ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ስታስቲክ አገለግሎት የኢኮኖሚ ቆጠራ አስተባባሪ አቶ ሀጎስ ሀይሌ የኢኮኖሚ ቆጠራ ስልጠና በሀገር አቀፍ ደረጃ በ54 የስልጠና ጣቢያዎች እየተሰጠ ሲሆን የሀገር አቀፉን የኢኮኖሚ ምጣኔ ክለሳ ለማድረግ የሚያገለግል መረጃ የሚሰበሰብበት መሆኑን አስታውቀዋል።
በስልጠና ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኩልፎ ካምፓስ ዲን ዶክተር ደግፌ አሰፋ፥ ስልጠናው መረጃን ከመሰብሰበ ባለፈ በሀገሪቱ ያሉ እውነታዎችንና የኢኮኖሚ ተግዳሮቶችን ለይቶ መረጃን መሰብሰብ ጠንካራ ኢኮኖሚን ለመገንባት ለሚደረጉ ጥናቶች ያግዛል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ስታስቲክ አገልግሎት አርባ ምንጭ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ስሜ አንበሴ በባለፈው አመት የግብርና ናሙና የተከናወነ ሲሆን በ2018 ደግሞ የኢኮኖሚ ቆጠራ ለማካሄድ ለዘርፉ ባለሙያዎች ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን አስታውቀዋል።
መረጃ የሀገር ሀብት በመሆኑ መረጃ ሰጪዎች ተክክለኛ መረጃ መስጠትና መረጃ ሰብሳቢዎችም በአግባቡ ትክክለኛ መረጃ በመሰብሰብ ለሀገር ተጠቃሚነት ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከሚገኙ ዞኖች 8ቱ በአርባምጭ ስታስቲክ አገልግሎት የሚካተቱ ሲሆን በ8ቱ ዞኖች ውስጥ ባሉ የከተማና ገጠር ቀበሌያት የኢኮኖሚ ቆጠራ እንደሚካሄድም ገልፀዋል ።
በአጠቃላይ ከ1ሺ 200 በላይ የዘርፉ ባለሙያዎች ለሚቀጥሉት 25ቀናት ሰልጥነው ወደ ቆጠራ እንደሚገቡ አስረድተዋል።
ዘጋቢ፡ ገነት መኮንን – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
More Stories
መረጃ ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሚናው የጎላ መሆኑ ተገለጸ
ተዓማኒና ወቅቱን የጠበቀ መረጃ ለሀገራዊ ውሳኔ ፋይዳው የጎላ መሆኑ ተገለፀ
ለጠቅላላ አገራዊ ምርት ግምት መሠረታዊ መረጃዎችን ለመሰብሰብ ለሚደረገው ጥረት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ተጠየቀ