መረጃ ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሚናው የጎላ መሆኑ ተገለጸ

መረጃ ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሚናው የጎላ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ መስከረም 05/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) መረጃ ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሚናው የጎላ መሆኑን የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት አስታወቀ

አገልግሎቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚካሄደው የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ለመስክ መረጃ ሰብሳቢዎች እና ተቆጣጣሪዎች በቦንጋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ስልጠና እየተሰጠ ነው።

በስልጠናው የተገኙት በኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት የፌደራል ስልጠና አስተባባሪ አቶ ካሳሁን መኩሪያ፥ በሳይንሳዊ ዘዴዎች የተሰበሰቡ መረጃዎች የአንድን ሀገር ኢኮኖሚያዊ እና ዴሞክራሲያዊ ልማት ለማፋጠን ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል።

ሀገራዊ የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ለማካሄድ በ55 የስልጠና ማዕከላት ለባለሙያዎች ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ተናግረው በቦንጋም ማዕከል የተጀመረው የዚሁ አካል እንደሆነ ጠቁመዋል።

በሁሉም ማዕከላት 43 ሺህ ሰልጣኞች ስልጠናውን እየወሰዱ መሆናቸዉን ጠቁመው ፤ ከስልጠናው በሚያገኙት ክህሎት መሠረት መረጃ ለመሰብሰብ ይሰማራሉ ብለዋል።

በቦንጋ የስልጠና ማዕከል ከካፋ ዞን ሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተመለመሉ ሰልጣኞች እየተሳተፉ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት የቦንጋ ስልጠና ማዕከል አስተባባሪ አቶ ሀብታሙ ካውሳ ናቸዉ።

የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ሀገራዊ ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ ሰልጣኞች በአግባቡ ተከታትለው ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የቦንጋ ስልጠና ማዕከል የቴክኒክ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተመስገን ጎሹ በበኩላቸው በቦንጋ ማዕከል 236 ሰልጣኞች እየሰለጠኑ መሆኑን ተናግረዋል።

ሰልጣኞች ስልጠና ካጠናቀቁ በኋላ በከተማና በገጠር በተለያዩ ስራ ዘርፎች የተሰማሩ ድርጅቶች ጋር በመድረስ መረጃ ይሰበስባሉ ብለዋል።

የካፋ ዞን ስራና ክህሎት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሚልዮን ኃይሌ፥ ሰልጣኞች መረጃ ለመሰብሰብ ወደ መስክ በሚሰማሩበት ወቅት ታዓማኒ መረጃ መሰብሰብ እንዳለባቸው አስገንዝበው ለዚህም ዞኑ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግም ገልጸዋል።

የቦንጋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ምክትል ዲን ወይዘሮ ለጢፋ አህመድ በበኩላቸው ሰልጣኞች በስልጠና ቆይታቸው የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ ኮሌጁ ያደርጋል ብለዋል።

የስልጠናው ዓላማ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ለማካሄድ የባለሙያዎች አቅም ማጎልበት መሆኑም ተገልጿል።

ዘጋቢ: ሀብታሙ ኃይሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን