ተዓማኒና ወቅቱን የጠበቀ መረጃ ለሀገራዊ ውሳኔ ፋይዳው የጎላ መሆኑ ተገለፀ
የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ሆሳዕና ቅርንጫፍ በክልሉ ከተለያዩ አካባቢዎች ለተውጣጡ ከ1 ሺ 100 በላይ ለሚሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ ስልጠና መስጠት ጀምሯል።
በኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የሆሳዕና ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ካሳሁን አሰፋ፤ ስልጠናው ለኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ መስክ ሰራተኞች በሀገር ዐቀፍ ደረጃ የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመው፤ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ደረጃ ስልጠናው የመጀመሪያ መሆኑን አመላክተዋል።
እንደ ክልል በሆሳዕና ከተማ 1 ሺ 100 በወራቤ ደግሞ 600 የዘርፉ ባለሙያዎች በስልጠናው እንደሚሳተፉ ገልፀዋል።
እንደ ሀገር ከ50 ሺ በላይ በሚሆኑ በተለያዩ አካባቢዎች ከ40 ሺ በላይ መረጃ ሰብሳቢዎች እንዲሁም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከ3 ሺ 400 በላይ አካባቢዎች 2 ሺ 200 የሚሆኑ መረጃ ሰብሳቢዎች እንደሚሰማሩ ተናግረዋል።
መረጃው በሀገሪቱ የተለያዩ አምራች ድርጅቶች ተጨባጭ መረጃ ለማሰባሰብ የሚረዳ ከመሆንም ባሻገር በዓለም ዐቀፍ የኢኮኖሚ ድርጅቶች ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል ነው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የመረጃ አሰባሰብ ሂደቱ በናሙና ሲሰራ የነበረ መሆኑን ጠቁመው፤ አሁን ሀገሪቱ ለምታወጣው የልማት ፖሊሲና በዘርፉ ለሚታቀደው እቅድ ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑንም አቶ ካሳሁን አመላክተዋል።
ስለጠናው ለሚቀጥሉት 25 ቀናት የሚዘልቅ መሆኑን የጠቆሙት ስራ አስኪያጁ፤ ጥራት ያለውን መረጃ ማሰባሰብ የሚያስችል እውቀት መቅሰሚያ መድረክ እንደመሆኑ ሠልጣኞችም ሆኑ አሰልጣኞች በስልጠና ቆይታቸው ወቅት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በስልጠናው ማስጀመሪያ ወቅት የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ የልማት መረጃና ስነ ህዝብ ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊና የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አብርሃም ዓለሙ በበኩላቸው፤ ተዓማኒና ወቅቱን ያገናዘበ የመረጃ ግብዓት ማግኘት ለተገቢ ሀገራዊ ውሳኔ የጎላ ሚና ያለው መሆኑን አመላክተዋል።
ስልጠናው በተለያዩ የአምራች እንዱስትሪዎችና የኢኮኖሚ ዘርፎች ተጨባጭ መረጃዎችን ለማግኘት የሚረዳ መሆኑን ጠቁመው፤ ዘርፉ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ቅንጅት የሚሻ መሆኑን ገልፀዋል።
ዘጋቢ: አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
መረጃ የሀገር ሀብት በመሆኑ ትክክለኛ መረጃ በመስጠት ሀገራዊ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል – የኢትዮጵያ ስታስቲክ አገልግሎት
መረጃ ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሚናው የጎላ መሆኑ ተገለጸ
ለጠቅላላ አገራዊ ምርት ግምት መሠረታዊ መረጃዎችን ለመሰብሰብ ለሚደረገው ጥረት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ተጠየቀ