ለጠቅላላ አገራዊ ምርት ግምት መሠረታዊ መረጃዎችን ለመሰብሰብ ለሚደረገው ጥረት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ተጠየቀ
ሀዋሳ፡ መስከረም 05/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ለጠቅላላ አገራዊ ምርት ግምት መሠረታዊ መረጃዎችን ለመሰብሰብ በሚደረገው ጥረት ላይ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ የዳዉሮ ዞን አስተዳደር አስታወቀ፡፡
በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የሶዶ ስታቲስቲክስ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ከመስከረም 5 ጀምሮ ለሚቀጥሉት 20 ቀናት የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ከዳዉሮና ኮንታ ዞኖች ለተወጣጡ ባለሙያዎችና አመራሮች ስልጠና እየሰጠ ነው።
የዳዉሮ ዞን ዋና አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ወንድሙ ወራቦ እንደገለፁት ትክክለኛና ተጨባጭ መረጃ ለአገር ከሚሰጠው ፋይዳ አኳያ ኃላፊነት የሚጠይቅ የልማትና የኢኮኖሚ አቅጣጫ እንዲወስኑ የሚያግዝ በመሆኑ በአገር ደረጃ በቁርጠኝነትና በጥብቅ ዲስፕሊን እየተሠራ ይገኛል።
ይህ የመረጃ አሰባሰብ ሥርዓት ውጤታማ ለማድረግ በተገቢው የሰው ኃይል በማደራጀት በክህሎትና በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ የሚያስችል ሥራም በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል።
ለጠቅላላ አገራዊ ምርት ግመታ ተጨባጭ መረጃ እንዲኖር መሠረታዊ መረጃዎችን ለማስገኘት የሚደረገው ጥረት የመስክ ባለሙያዎች በኃላፊነት እንዲሠሩም ጠይቀዋል።
የዞኑ ሥራና ክህሎት መምሪያ ኃላፊ አቶ ባቲሣ ዋጌሾ በበኩላቸው ባለሙያዎች በአገራዊ አጀንዳና ለአገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት የድርሻቸውን ሊወጡ የሚችሉ የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ላይ ሰልጣኞች በኃላፊነት የተጣለባቸውን ተግባር መወጣት ይገባል ብለዋል።
በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ዳዉሮ ታርጫ ካምፓስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ እንግዱ ካሱ በበኩላቸው ለትክክለኛ አገራዊ ፖሊሲ የሚጠቅሙ መረጃዎችን በመሰብሰብና በማደራጀት በኩል እየተደረገ ያለው ተግባር ውጤታማ እንዲሆን በተቀናጀ ጥረት ሊሠራ ይገባል፡፡
አሁን ላይ ሰልጣኞች የተጣለባቸውን ኃላፊነት በመረዳት ለቀጣይ አገራዊ ኢኮኖሚ የሚጠቅሙ ተግባራትን ማከናወን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በቀጣይ ለሚከናወኑ ተግባራት የሚያግዙ ድጋፎች በተቀናጀ ሁኔታ እንደሚደረጉም የሥራ ኃላፊዎች ገልጸዋል።
የሶዶ ስታቲስቲክስ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደርዘኔ ደግፌ በበኩላቸው ስልጠናው ለሚቀጥሉ 20 ቀናት የሚሰጥ በመሆኑ ሰልጣኞች በዲስፕሊን እንዲከታተሉም ጠይቀዋል።
እንደአገር ከ55 ሺህ በላይ የቆጠራ ጣቢያዎች ሲኖሩ በ55 የሥልጠና ጣቢያዎች ከ40 ሺህ በላይ የመስክ ባለሙያዎች ሥልጠናውን የሚካፈሉ ሲሆን እንደ ዳዉሮና ኮንታ በአንድ የሥልጠና ማዕከል 245 ስልጠኞች ስልጠናውን የሚወስዱ ይሆናል።
ዘጋቢ፡ መሣይ መሠለ – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
መረጃ የሀገር ሀብት በመሆኑ ትክክለኛ መረጃ በመስጠት ሀገራዊ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል – የኢትዮጵያ ስታስቲክ አገልግሎት
መረጃ ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሚናው የጎላ መሆኑ ተገለጸ
ተዓማኒና ወቅቱን የጠበቀ መረጃ ለሀገራዊ ውሳኔ ፋይዳው የጎላ መሆኑ ተገለፀ