ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት የበለፀገች ሀገር ለመገንባትና አንድነትን ለማጠናከር አጋዥ መሆኑ ተገለፀ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ የባስኬቶ ዞን ወጣቶች ክንፍ “በጎነት ለአብሮነትና ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል በኣሪ ዞን ጂንካ ከተማ ወሰን ተሻጋሪ በጎ ተግባራት አከናዉነዋል።

የበጎ አድራጎቱ ቡድኑ በቆይታው የችግኝ ተከላ፣ የአቅመ ደካማ ቤት ግንባታና የቤት ቁሳቁስ ድጋፍና ለተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ያተበረከ ሲሆን በጂንካ ከተማ የተሰሩ የኮሪደር ልማት ስራዎች ጉብኝት አካሂዷል።

የኣሪ ዞን ረዳት የመንግስት ተጠሪና የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካና ህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ማናኩል ሳህሎ በመርሃ ግብሩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች እያከናወኑት ያለዉ ወሰን ተሻጋሪ የበጎ አገልግሎት ተግባር የሀገራችን ከፍታና ማንሰራራትን የሚያጎሉ ስለሆኑ ሊበረታቱ እንደሚገባ ገልፀው የባስኬቶ ዞን ወጣቶች በዞኑ መጥተዉ ላከናወኑት የበጎ ተግባር ስራዎች አመስግነዋል።

የበጎ ተግባር አገልግሎት መልካም ተግባራትን ከማከናወን ባሻገር የእርስ በርስ ግንኙነትን የሚያጠናክር በመሆኑ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህላችንን በሚገባ ልናሰፋው ይገባል ያሉት የባስኬቶ ዞን ረዳት የመንግስት ተጠሪና የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካና ህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ክንዴ ፍሬዉ ናቸው።

የባስኬቶና የኣሪ ዞን ብልፅግና ፓርቲ የወጣቶች ክንፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ዕድሉ ከበደ እና አቶ እስራኤል አዳሙ በጋራ እንደገለፁት፤ ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋት የበለፀገች ሀገር ለመገንባትና አንድነትን ለማጠናከር ስለሚያግዝ በትኩረት እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

ወጣቶች የማህበረሰቡን አንድነትና ሕብረትን ለማጠናከር ምሳሌ በመሆን ጊዜውንና ጉልበቱን ለመልካም ተግባር ማዋል እንዳለበት በበጎ አገልግሎቱ የተሳተፉ ወጣቶች ገልፀዋል።

ዘጋቢ፡ ተመስገን አሰፋ – ከጂንካ ጣቢያችን