የኅብር ቀንን ስናከብር ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጎልበት ሊሆን እንደሚገባ ተገለጸ

የኅብር ቀንን ስናከብር ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጎልበት ሊሆን እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ጷጉሜን 2/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኅብር ቀንን ስናከብር ብዝኃነትን ያከበረ፣ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጎልበት ሁላችንም በጋራ ለመስራት ቃል በመግባት ሊሆን እንደሚገባ ተገለጸ።

ዕለቱን በማስመልከት በቤቶ ከተማ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ተካሄዷል።

በጎፋ ዞን የበቶ አንድነት በጎ ሥራ ማህበር አዘጋጅነት “ጤናዬን እጠብቃለሁ፣ ለአረጋዊያን እሮጣለሁ” በሚል መሪ ቃል 4ኛው ዙር የጎዳና ላይ ሩጫ በድምቀት ተካሄዷል።

ውድድሩን ያስጀመሩት የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ የኅብር ቀንን ስናከብር ብዝኃነት የኢትዮጵያ ጌጥ፣ ዉበትና የጥንካሬያችን ምንጭ መሆኑን በመገንዘብ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የቤቶ አንድነት ማህበር ያዘጋጀው የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ከጤና ጥቅሞች በተጨማሪ ገቢው ለበገ ዓላማ አረጋዊያንን ለመርዳት በመሆኑ የወጣቶች ተነሳሽነት ለህብረ ብሄራዊ አንድነት አበርክቶው የላቀ ስለመሆኑ አስገንዝበዋል።

የዞኑ የመንግስት ዋና ተጠሪና የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጋሻለው በበኩላቸው የኅብር ቀንን ስናከብር ፣ ብዝኃነትን ያከበረ፣ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጎልበት ሁላችንም በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል።

የቤቶ አንድነት ማህበር ያዘጋጀው ውድድር የወንድማማችነትና የእህትማማችነት እሴቶችን ለማጠናከርና ሰው ተኮር ዓላማ ያነገበ ስለመሆኑ አብራርተዋል።

የበቶ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ያለው ያማ በበኩላቸው በጋራ ሕልም የጋራ ሀገራችንን ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሻገር የበኩላችንን ለማበርከት ቃላችንን የምናድስበት ነው ብለዋል።

ከውድድሩ የሚገኘው ገቢ አቅመ-ደካማ፣ አረጋዊያን እና ጧሪ ቀባሪ ላጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ እና በበዓላት ወቅት ማዕድ ለማጋራት እንደሚውል ጠቁመዋል።

የበቶ አንድነት በጎ ሥራ ማህበር ሰብሳቢ አቶ ኤፍሬም ገዛኸኝ ማህበሩ ከተለያዩ አካላት 200 ሺህ ብር በመሰብሰብ ረዳት ለሌላቸው ለ325 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ በማዘጋጀትና ለ350 አረጋዊያን የበዓል መዋያ ማዕድ ለማጋራት ታቅዶ ፐሮግራሙ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በውድድሩ አሸናፊ ለሆኑ ተሳታፊዎች የማበረታቻ ምስክር ወረቀትና መዳሊያ ከዕለቱ የክብር እንግዶች ተበርክቶላቸዋል።

በውድድሩ አሸናፊ የሆኑት ወጣት ሙሉቀን ሞርጋማ እና ወጣት መክሊት ዳመነ በሰጡት አስተያዬት ለበጎ ዓላማ ተነሳስተን በመሮጥ አሸናፊ በመሆናችን ደስተኞች ነን ብለዋል።

በውድድሩ የዞንና ክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የከተማው አስተባባሪ አካላትን ጨምሮ ከ5 ሺህ በላይ ከተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን