የታላቁ የኢትዮጲያ ህዳሴ ግድብ ስራው ተጠናቆ ለምረቃ መድረሱ እንዳስደሰታቸው በጉራጌ ዞን የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ
የዞኑ ህዝብ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስከ አሁን ከ 77 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታውቋል።
በመላው የኢትዮጲያ ህዝብ የገንዘብ፣ የላብና የደም ጠብታ የተገነባው የታላቁ የኢትዮጲያ ህዳሴ ግድብ ተጠናቆ ለምረቃ መዘጋጀቱ ይታወቃል።
በወልቂጤ ከተማ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎችም ያደረጉትን አስተዋፅኦ ለፍሬ ደርሶ በማየታቸው ደስታቸውን ገልፀዋል።
ካነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወ/ሮ ሂክማ አብዶ እና አቶ አሚን ጀማል ይገኙበታል፤ ሁለቱም በሰጡት አስተያየት ከጅምሩ አንስቶ የቦንድ ግዢን ጨምሮ በልዩ ልዩ መልኩ ለህዳሴው ግድብ መገንባት የራሳቸውን አበርክቶ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በዚህም ዛሬ ላይ የዘመናት ህልምና ምኞታቸው ተሳክቶ በማየታቸው ደስ እንደተሰኙ ነው የተናገሩት።
ነዋሪዎቹ በማከልም እኛ ኢትዮጲያዊያን በጋራ ከቆምን የቱንም ጉዳይ ከዳር ማድረስ እንደምንችል ማሳያችን ነው ሲሉም አብራርተዋል።
በመሆኑም የሃገር ኢኮኖሚ ከፍ እንዲል ከማድረጉም ባለፈ ቀጣይ በሃገራችን ይስተዋል የነበረውን የመብራት መቆራረጥና የሃይል እጥረት ችግር ተቀርፎና ለዘመናት በጭስ ይሰቃዩ ነበሩ እናቶች ስቃይ ያበቃል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልፀዋል።
በጉራጌ ዞን አስተዳደር የኢኮኖሚ ማህበራዊና መሰረተ ልማት ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ አቶ ሙላት ሸሪፍ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ስራው ከመበሰሩ ጀምሮ በዞኑ የማስተባበሪያ ምክር ቤት በማቋቋም የዞኑ ህዝብ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የራሱን አስተዋፅኦ ማድረጉን ተናግረዋል።
ማንኛውም ፕሮጀክት ካለህዝብ ተሳትፎ ሊሳካ አይችልም ያሉት አቶ ሙላት በተለይ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የሃገር ምልክት መሆኑን ገልፀው ይህን የተረዳው የዞኑ ህዝብም በንቃትና በደስታ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱንም አብራርተዋል።
ሠራተኛው ከደመወዙ፣ አርሶአደሩ ከምርቱና ከገንዘቡ፣ ባለሀብቱ ከጥሪቱ ለግድቡ ግንባታ በመለገስ አሻራውን ማኖሩና ይህም የፅናት ምልክት ማሳያ ጭምርም ነው ያሉት።
በመሆኑም እስከ 2017 ዓ/ም ከመንግስት ሰራተኛ 69 ሚልዮን 170 ሺህ 787 ብር የቦንድ ግዢና ከሌላው ማህበረሰብም እንዲሁ ቦንድ ግዢ 7 ሚልዮን 423 ሺህ 984 ብር መፈፀሙን ያወሱት የዳይሬክቶሬቱ ቡድን መሪ፥ በስጦታ ደግሞ የተበረከተው 584 ሺህ 461 ሲሆን አጠቃላይ በዞኑ 77 ሚልዮን 149 ሺህ 265 ብር ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ገቢ መደረጉንም ነው የገለፁት።
በተለይም የህዳሴ ዋንጫ በየወረዳው ይዘዋወርበት በነበረ ጊዜ በዞኑ ጌታ ወረዳ የሚገኙ አንዲት አርሶ አደር የአንድ መቶ ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን ለአብነት ያነሱት አቶ ሙላት በሁሉም ማህበረሰብ ዘርፍ መሰል አበርክቶ ተደርጓልም ብለዋል።
ግድቡ የጋራ የወል ትርክትን የፈጠረ እና በቀጠናው ትብብርና ትስስርን የሚያጠናክር መሆኑንም ነው የተናገሩት ።
በተጨማሪም የኢትዮጵያን በዓለም መድረክ የሚኖራትን ተሰሚነት ከፍ የሚያደርግና ብልፅግናዋን የሚያፋጥን ስለመሆኑም አስረድተዋል።
እንደህዳሴ ግድብ ሁሉ ሌሎች ፕሮጀክቶችን ጀምሮ ለመጨረስ የህዝቡ ትብብር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባልም ብለዋል የዳይሬክቶሬቱ ቡድን መሪ።
የሃገርን ብሔራዊ ጥቅም፣ ክብርና ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ የውስጥ አንድነት፣ መደማመጥ፣ መከባበርና ለሠላም ቅድሚያ መስጠት ከመላው ኢትዮጵያዊ ይጠበቃል ሲሉም አቶ ሙላት ተደምጠዋል።
ታላቁ የህዳሴ ግድብ እንደሃገር የመቻል መንፈስ የተንፀባረቀበት፣ ሃገራዊ አንድነት ያጠናከረ ከዚያም ባለፈ የኢትዮጲያ ህዝብ በተባበረ ክንድ የትኛውም ጉዳይ ጀምሮ መፈፀም እንደሚችል ለአለም የታወጀበት የጋራ አሻራ ውጤት ነው ሲሉም ተደምጠዋል።
በቀጣይም በሌሎችና መሰል ግዙፍ ሃገራዊ ፕሮጀክቶች ላይም የህዝቡ አስተዋፅኦ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባልም ብለዋል።
ዘጋቢ፡ ሚፍታ ጀማል – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
ከተስፋ ወደ ሚጨበጥ ብርሀን ለመሻገር በተሰሩ ተግባራት ውጤት ማምጣት መቻሉ ተገለጸ
የኅብር ቀን ለኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን የኣሪ ዞን አስተዳደር ገለጸ
የህብር ቀን “ብዝሃነት የኢትዮጵያ ጌጥ” በሚል መሪ ሐሣብ በማዕከላዊ ኢትዮያውያ ክልል ሣጃ ክላስተር እየተከበረ ነው