በቀሪ ጊዜ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆችን ወደትምህርት ገበታ በማምጣት ወላጆች የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ ጥሪ ቀረበ

በቀሪ ጊዜ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆችን ወደትምህርት ገበታ በማምጣት ወላጆች የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ ጥሪ ቀረበ

ሀዋሳ፡ ጷጉሜን 02/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በቀሪ ጊዜያት እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆችን ወደትምህርት ገበታ በማምጣት ወላጆች የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ የቤንች ሸኮ ዞን ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።

የ2018 ትምህርት ዘመን ምዝገባ ከተጀመረ ነሐሴ አስራ ዘጠኝ ጀምሮ የተመዘገቡ ተማሪዎች አሀዝ 64 ከመቶ ብቻ መመዝገባቸው የተገለጸ ሲሆን፥ የ2018 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ስራው ከመስከረም 05/2018 ጀምሮ በይፋ እንደሚጀመር የወጣ መረሀግብር ያመላክታል።

በቤንች ሸኮ ዞን በ2018 ትምህርት ዘመን በየደረጃው በሚገኙ የትምህርት እርከኖች 199ሺ 876 ያህል ተማሪዎች በ277 ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን እንደሚጀምሩ ለዚሁም አስፈላጊውን ዝግጅት አድርገው ወደተግባር መግባታቸውን የትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አገኘው ወርቁ ተናግረዋል።

ከነሐሴ አስራ ዘጠኝ ጀምሮ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ምዝገባ በይፋ መጀመሩን የተናገሩት አቶ አገኘው፥ እስካሁን ባለው ሂደት የተመዘገቡት 130ሺ 773 ተማሪዎች ብቻ መሆናቸውን እና የእቅዳቸው 64 ከመቶ ብቻ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በተለይ በዘንድሮ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረው፥ ህጻናት ወደትምህርት ገበታ እንዲመጡ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ጠቁመው ወላጆችም እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናትን ወደ ትምህርት ገባታ እንዲመጡ በማድር በኩል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በተለይም በግል ትምህርት ቤቶች የተማሪ ምዝገባ ወደኋላ መቅረቱን ጠቁመው በሚዛን አማን ከተማ በሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች እስካሁን የተመዘገቡት የተማሪዎች አሀዝ 50 ነጥብ 4 ከመቶ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ስለዚህም ይላሉ አቶ አገኘው፥ የመማር ማስተማሩ ተግባር በይፋ ከመስከረም አምስት 2018 ጀምሮ የሚካሄድ በመሆኑ ባሉት ቀሪ ቀናቶች ወላጆች ከመዘናጋት ወጥተው ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት በማምጣት ማስመዝገብ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ዘጋቢ: አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን