ህብረተሰቡ ፍትሃዊ፣ ቀልጣፋ እና ጥራት ያለውን ልማት እና መልካም አስተዳደር ተጠቃሚ እንዲሆን የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ የጀመረውን ዘመናዊና ሳይንሳዊ አሰራርን አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት ተገለጸ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ፕላንና ልማት ቢሮ በ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸምና 2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ በሆሳዕና ከተማ የምክክር መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ የተገኙት የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቴዎስ አኒዮ በዞኑ የተለያዩ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው በተለይም በዞኑ ሰላም ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል።
ለገጠርና ከተማ ግብርና ተግባር በተሰጠው ትኩረት በዘንድሮ ዓመት በቂ የማዳበሪያ እና የምርጥ ዘር ግብአት ስርጭት መደረጉንም ገልጸዋል።
በመንግስት እና በህብረተሰብ ተሳትፎ በተገኘው ከ7 ቢሊዮን በሚበልጥ ወጪ የአስፋልት እና የኮርደር ልማት ጨምሮ የተለያዩ መሰረተ ልማት ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ከአቶ ማቴዎስ ገለጻ ለማወቅ ተችሏል።
በመሆኑም ከተማው የቱርዝም ማዕከል ለማድረግ በሚያስችል ደረጃ እያደገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ባዩሽ ተስፋዬ ባደረጉት ንግግር ቢሮው የረጅም፣ የመካከለኛ እና የአጭር ጊዜ ዕቅድ በማዘጋጀትና ስለተግባራዊነቱም ክትትልና ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።
ተቋሙ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ጂኦስፓሻልና ዲሞግራፊያዊ መረጃዎችን በመሰብሰብ እና በመተንተን ለታለመለት ዓለማ እንዲውል ለባለድርሻ አካላት የማዳረስ ሚና እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
የመረጃ ክፍተቶችን ለመሙላት የሚያስችሉ ጥናቶችን በማድረግ ከማክሮ ኢኮኖሚ ፊስካል ፖሊስ ጋር የተያያዙ ጥናቶችን በማካሄድ በክልል የሚተገበሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ዕቅዶች በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑንም ዶክተር ባዩሽ ተናግረዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በክልሉ ፕሬዚዳንት ኢንሼቲቭ መነሻ ከክልሉ ፖሊሲ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የክልሉን የልማት አቅም፣ የቁጠባና ኢንቨስትመንት ጥናት ስራዎች የተጠናቀቁ ሲሆን የመንገድ ኔትወርክ ጥናት ስራም በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል ብለዋል።
የክልሉን ሀብት ግመታ ሰነድ (RGDP) የኢኮኖሚ ዕድገት የሚገልጽ የጥናት ሰነድ በማዘጋጀት ለባለድርሻ አካላት ተደራሽ የማድረግ ስራ መሰራቱንም ገልጸዋል።
የስነ ህዝብ በጎና አሉታዊ ተጽዕኖ ለይቶ የሚያሳይ ጥናት ተደርጎ ለስነ ህዝብ ምክር ቤት ከቀረበ በኃላ ወደ ትግበራ መገባቱንም ዶክተር ባዩሽ አብራርተዋል።
በመድረኩ በክብር እንግድነት የተገኙት የፕላን መሰረተ ልማትና የመንግስት ሀብት አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ታመነ ገብሬ በበኩላቸው ህብረተሰቡ ፍትሀዊ፣ ቀልጣፋ እና ጥራት ባለው ልማት እና መልካም አስተዳደር ተጠቃሚ እንዲሆን ቢሮው የጀመረውን ዘመናዊና ሳይንሳዊ የመረጃ አደረጃጀትን፣ አሰባሰብ፣ ጥናትና ትንታኔን የበለጠ አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግር የመፍታት ተልዕኮ የተሰጠው እንደመሆኑ ሚናውን እየተወጣ ያለ ተቋም ነው ብለዋል።
ተጀምረው ያለተጠናቀቁ እና የህብረተሰብ ጥያቄ ሆነው የቆዩ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ ተቋሙ ተገቢ ክትትል አድርጓል ሲሉም አቶ ታመነ ጠቁመዋል::
በመድረኩ በ2017 በጀት አመት የዕቅድ አፈጻጸም እና በ2018 ዕቅድ ዙሪያ ዝርዝር ሀሳብ የያዘ ሰነድ ቀርቦ ውይይት የተደረገ ሲሆን የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ተቋማት የዕውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በመድረኩም በክልሉ ከሚገኙ ከሁሉም ዞኖች ፣ልዩ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ፕላንና ልማት ሴክተር ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ፡ ሳሙኤል መንታሞ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የህብር ቀን “ብዝሃነት የኢትዮጵያ ጌጥ” በሚል መሪ ሐሣብ በማዕከላዊ ኢትዮያውያ ክልል ሣጃ ክላስተር እየተከበረ ነው
የታላቁ የኢትዮጲያ ህዳሴ ግድብ ስራው ተጠናቆ ለምረቃ መድረሱ እንዳስደሰታቸው በጉራጌ ዞን የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ
በቀሪ ጊዜ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆችን ወደትምህርት ገበታ በማምጣት ወላጆች የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ ጥሪ ቀረበ