በትምህርት ዘርፍ የተገኙ ውጤቶችን አጽንቶ ማስቀጠል እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ፀሐይ ወራሳ ገለፁ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ለአንደኛ ደረጃ መምህራንና ትምህርት ቤት አመራሮች ከዩኒሴፍ የትምህርት ፕሮግራም ጋር በመተባበር በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት አተገባበር ላይ የተዘጋጀ አቅም ግንባታ ስልጠና መድረክ በጂንካ ከተማ በተጀመረበት ወቅት ነው የቢሮ ሀላፊዋ ይህንን የገለፁት።
በዛሬው ዕለት ጳጉሜን 1 – የጽናት ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከብር ሲሆን በሁሉም መስክ ያሳካናቸውን አጽንተን ልንቀጥል ይገባናል ያሉት መድረኩን በንግግር የከፈቱት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ፀሐይ ወራሳ ናቸው።
በትምህርት ዘርፍ የተገኙ ድሎችን አጽንተን ማስቀጥል እንደሚገባም ወ/ሮ ፀሐይ አሳስበዋል።
ያሳካናቸው ድሎችን አጽንተን መቀጠል የምንችል ህዝቦች መሆናችንን ዓለም እንዲገነዘብ ሁላችንም አምባሳደር መሆን አለብን ሲሉም ገልፀዋል።
ከዚህ በፊት የትምህርት ሥርዓቱ ጉድለት ያለበት እንደነብር ያስታወሱት የቢሮ ሀላፊዋ፤ በአሁን ወቅት በትምህርት ጥራትና ውጤት ዘርፍ ጅምር ውጤቶች እየተመዘገቡ መጥተዋል ብለዋል።
127 ሚሊዮን ብር ከህዝቡ እንዲሁም የክልሉ መንግስት ተጨማሪ 1 መቶ ሚሊዮን ብር በጀት መድቦ በአምስት የትምህርት ዓይነቶችና በ15 በአፍ መፍቻ ቋንቋ መጽሐፍት እንዲታተም ተደርጎ በቅርቡ ሙሉ በሙሉ ወደ ትምህርት ቤቶች ይደርሳል ብለዋል ወ/ሮ ፀሐይ።
የትምህርት ጥራትና ውጤት በዘላቂነት እንዲጠበቅ ከህዝቡ ጋር በቅንጅት የመሥራት ሂደት ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም ገልፀዋል።
በ2018 የትምህርት ዘመን በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ እንዲመራ ከዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥም የቢሮ ሀላፊዋ አሳስበዋል።
ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ ከ73 በመቶ በላይ በትምህርት ልማት ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ስልጠና እንዲያገኙ መደረጉን የገለፁት የቢሮው ምክትልና የመምህራን ልማት ዘርፍ ሀላፊ ዶ/ር ታምራት ይገዙ፤ መምህራንና የትምህርት አመራሮች ከ99 በመቶ በላይ የክረምት ስልጠና እንዲያገኙ መደረጉን አስረድተዋል።
አዲሱ ሥርዓት ትምህርት የ21ኛ ክፍለ ዘመን ብቃት ላይ የተመሠረተ፣ ብቃት ተኮር፣ ሀገር በቀል እውቀቶችን መነሻ አድርጎ ከውጭ በዘርፉ ውጤት መመዝገብ የሚያስችሉ ሐሳቦች የተወሰደ እና ከሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ጋር የሚያያዝ የቀለም ትምህርትን ከሙያ ጋር የሚያስተሳስር ነው ሲሉም ዶ/ር ታምራት አብራርተዋል።
ስልጠናው በዋናነት ለምን፣ ምን፣ እንዴት፣ ማን፣ በምን ያስተምራል የሚሉ ጥያቄዎችን መሠረተ ያደረገ እንደሆነም ገልፀዋል።
በመድረኩ በክልሉ ስር ከሁሉም መዋቅሮች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።
የስልጠና መድረኩ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ተከታታይ ቀናት በቡድን ተከፋፍሎ እንደሚሰጥ ታውቋል።
ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ እያስመዘገበች ላለችው የዕድገት ጉዞ ቀጣይነት የትምህርት ተቋማት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ለትምህርት ጥራት በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል ሲል የጋሞ ዞን አስተዳደር አሳሰበ
በኮንታ ዞን ጳጉሜን 1 – የጽናት ቀን በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል
በዞኑ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ሠላም ወሳኝ መሆኑን የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳደር ገለጸ