ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ እያስመዘገበች ላለችው የዕድገት ጉዞ ቀጣይነት የትምህርት ተቋማት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ለትምህርት ጥራት በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል ሲል የጋሞ ዞን አስተዳደር አሳሰበ

ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ እያስመዘገበች ላለችው የዕድገት ጉዞ ቀጣይነት የትምህርት ተቋማት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ለትምህርት ጥራት በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል ሲል የጋሞ ዞን አስተዳደር አሳሰበ

ፓርክላንድ ኮሌጅ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ከ1 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በዲፕሎማ አስመርቋል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የኮሌጁ ባለቤትና ፕሬዚዳንት ዕጩ ዶ/ር ቴዎድሮስ ፋንታሁን፤ የፓርክላንድ ኮሌጅ በዕውቀት የዳበረ በስነ-ምግባር የታነጸ የተማረ የሰው ኃይል በማፍራት አገራዊ ግዴታውን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።

በዕለቱ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ከ 1 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በዲፕሎማ አስመርቋል ያሉት የኮሌጁ ፕሬዚዳንት፤ ከመማር ማስተማር ተግባር በተጨማሪ በሃገር አቀፍ፣ በክልልና በዞን ደረጃ የሚደረጉ የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶች ላይ በሰፊዉ እየተሳተፈ ይበል የሚያሰኝ ስራ መስራቱንም ገልጸዋል።

የዕለቱ የክብር እንግዳ እና የጋሞ ዞን አስተዳደር የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊና የአስተዳደሩ ተወካይ አቶ ጣሰው ከበደ፤ ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ እያስመዘገበች ላለው የዕድገት ጉዞ ቀጣይነት የትምህርት ተቋማት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ለጥራት በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ተመራቂዎች ባገኙት ዕውቀት ማህበረሰቡን በቅንነት በማገልገል በመፍጠር እና በመፍጠን መርህ ተግተው እንዲሰሩ አደራ ብለዋል።

የጋሞ ዞን ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና መምሪያ ኃላፊ አቶ ወንድሙ ኡቶ በሰጡት የስራ መመሪያ፤ ተመራቂ ተማሪዎች በቀጣይ የትምህርት ደረጃቸውን በማሻሻል እና ስራ ፈጣሪ በመሆን ለራሳቸውም ሆነ ለሌሎች የስራ ዕድል በመፍጠር ኃላፊነታቸውን እንደወጡ አደራ ብለዋል።

ከዕለቱ የማዕረግ ተመራቂዎች መካከል ብርቱኳን አየለ እና አማረች ቃዌ፤ የህዳሴ ግድቡ በተጠናቀቀበት ወቅት መመረቃቸው እንዳስደሰታቸው ገልፀው በቀሰሙት ዕውቀት ማህበረሰቡን ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ነው የገለፁት።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ በአርባ ምንጭ ከተማ ብሎም በጋሞ ዞን በኢኮኖሚያዊ እና በማህበራዊ ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋናና ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።

ዘጋቢ: አዕላፍ አዳሙ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን