በኮንታ ዞን ጳጉሜን 1 – የጽናት ቀን በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል

በኮንታ ዞን ጳጉሜን 1 – የጽናት ቀን በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል

በዞኑ የሚገኙ የሰላምና ፀጥታ አካላት ቀኑን “ጽኑ መሠረት ብርቱ ሀገር” በሚል መሪ ቃል በፓናል ውይይትና በትርዒት አክብረዋል።

በቦታው የተገኙት የዞኑ ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ገዛኸኝ ገዝሙ፤ ብልፅግና ፓርቲ ሀገሪቱን መምራት ከጀመረ ወዲህ ባለፉት ሰባት ዓመታት ዘርፈ ብዙ የውጭና የውስጥ ፈተናዎችን እያለፈ ተጨባጭ ውጤቶችን በማስመዝገብ ለኢትዮጵያዊያን ኩራትና ለአፍሪካውያን ተምሳሌት የሆነች ሀገር በመገንባት ላይ ይገኛል ብለዋል።

በዘንድሮው ዓመት በጳጉሜን 1 የሚከበረው “የጽናት” ቀን ኢትዮጵያ ጸንታ በመቆም ውጤቶችን እያሳየች በመሆኗ የፀጥታ አካላትና ሌሎች አካላት በየተሰማሩበት ድርሻቸው አጠናክረው እንዲቀጥሉ አስገንዝበዋል።

የዞኑ ሰላም፣ ፀጥታና ሚሊሻ መምሪያ ኃላፊ አቶ እስራኤል ጮንቄ ባቀረቡት መወያያ ጽሁፍ፤ የኢትዮጵያ የጽናት ተምሳሌትና ምልክት የሆኑት የፀጥታ አካላት ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ፀጥታ ጉልህ ሚና ሲወጡ የቆዩ መሆናቸውን ገልፀው ይህንንም አጠናክሮ በመምራት ሀገሪቱ ፀንታ በመቆም ውጤታማ ድሎች እየተመዘገቡ ይገኛል ብለዋል።

የፀጥታ አካላት በጽናት ቆመው ሲወጡ የነበረው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ይህም በሁሉ አቀፍ ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊመራ እንደሚገባ ገልፀዋል።

የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች በሀገሪቱ እየመጡ ያሉ ለውጦችንና ልማቶችን ለማስቀጠል የፀጥታ አካላት በበለጠ አቅምና ፅናት ሊሰሩ እንደሚገባ አመላክተው እንደመንግስትም ለፀጥታ አካላት የተሰጠው ትኩረት በበለጠ እንዲጠናከር አመላክተዋል።

የበዓሉ ተሳታፊዎች የዘንድሮ ጳጉሜ ቀናት ሲከበሩ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በሚመረቅበት ወቅት በመሆኑ ደስታ እንደፈጠረባቸውም አንስተዋል።

ዘጋቢ፡ ፋሲካ ሙሉጌታ – ከዋካ ጣቢያችን