በዞኑ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ሠላም ወሳኝ መሆኑን የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳደር ገለጸ

በዞኑ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ሠላም ወሳኝ መሆኑን የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳደር ገለጸ

በደቡብ ኦሞ ዞን በሐመር ወረዳ ዲመካ ከተማ በአካባቢው በሠላም ጉዳይ ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎ መግባባት ላይ እንደተደረሰ ተገልጿል፡፡

ማንኛውም ዜጋ ያለሥጋት ወጥቶ እንዲገባ፣ ማህበራዊ ክንዋኔዎችን ተረጋግቶ እንዲፈፅም ሠላም የማይተካ ሚና እንዳለው ተመላክቷል፡፡

በእለቱ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማልካ፤ በዞኑ የተጀመሩ ሰፊ የልማት ሥራዎች ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ሰላም ወሳኝ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ለሠላም እንቅፋት የሆኑትን ጉዳዮች ለመፍታት ሰፊ ስራዎች ተሰርተው ተጨባጭ ለውጦች መምጣታቸውን የገለጹት አስተዳዳሪው፤ ወንጀል ሰርተው የተሰወሩ ተጠርጣሪዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለህግ በማቅረብ ወደ ልማት ሥራ እንደሚገቡ ገልጸዋል፡፡

በሐመር ወረዳ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ለ10 ዓመታት የተለያዩ ወንጀሎች ሲሰሩ የነበሩ 57 ተጠርጣሪዎችን በህግ ቁጥጥር ሥር በማድረግ በእያንዳንዱ ላይ ውሳኔ እንደተሰጠ የሐመር ወረዳ ምክትል አስተዳደርና የሠላምና ጸጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኡቲና አሪ ገልጸዋል፡፡

ትምህርት፣ ጤና፣ የግብርና ሥራ እና ሌሎችን መንግስት ለማህበረሰቡ በተሻለ ደረጃ አገልግሎት እንዲሰጥ ሠላም ወሳኝ ስለሆነ ማህበረሰቡ ይህንን በመገንዘብ ለሠላም ዘብ መቆም እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በውይይቱ ተገኝተዉ አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል ባላባት ኦርጎ ወንጌላ እና የሀገር ሽማግለ አቶ ወንከ አረጋ፤ የሐመር ማህበረሰብ እንግዳ ተቀባይ፣ ያለውን አብልቶ አጠጥቶና አሳድሮ በሠላም የሚሸኝ መልካም ባህል ያለውን ለማጠልሸት የሚጥሩ ወንጀለኞች ላይ የተጀመረውን ህግ ማስከበር ማህበረሰቡ ከመንግስት ጎን እንደሚቆም ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠርጣሪዎችን አሳልፎ ለመስጠት ከቀበሌ የመጡ ባለድርሻ አካላት የመግባቢያ የጋራ ሰንድ ፈርመዋል፡፡

በመድረኩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሠላምና ፀጥታ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ በቀለ ሎኮሮማ፣ የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ፣ የሐመር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ጋርሾ፣ የዞን ከፍተኛ አመራሮች፣ የጸጥታ አካላት፣ ባላባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎችም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተው ሰፊ ጥያቄና አስተያየት ተሰጥቶ ተጠናቋል፡፡

ዘጋቢ፡ ታገል ለማ – ከጂንካ ጣቢያችን