ከግል ትምህርት ተቋማት በተለያየ ሙያ መስክ ሰልጥነው የሚወጡ ተማሪዎች በተማሩበት ሙያ ሥራን በመፍጠር ረገድ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለፀ

ከግል ትምህርት ተቋማት በተለያየ ሙያ መስክ ሰልጥነው የሚወጡ ተማሪዎች በተማሩበት ሙያ ሥራን በመፍጠር ረገድ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለፀ

‎ፓራሜድ ኮሌጅ አርባምንጭ በተለያዩ ሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 190 ተማሪዎችን አስመርቋል።

‎በምረቃ መርሀ ግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኮሌጁ ዲን አያልቅበት ብርሃኑ (ዶ/ር)፤ ትምህርት ለሰው ልጆች ሁለንተናዊ ዕድገት ወሳኝ በመሆኑ ሀገራችን የትምህርት ስብራት በመጠገን ጥራትን ለማስጠበቅ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።

‎ፓራሜድ ኮሌጅ ላለፉት 18 ዓመታት ተማሪዎችን ተቀብሎ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና፣ በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ መርሐግብር፣ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ተማሪዎችን አሰልጥኖ በማስመረቅ የተማረ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።

‎በ2015 ዓ.ም በተጀመረው የመውጫ ፈተና ተማሪዎችን አስፈትኖ በማሳለፍ ስመ ጥር ከሆኑት የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል ፓራሜድ ኮሌጅ አንዱ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር አያልቅበት፤ በዛሬው በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና መርሐግብር በዲፕሎማ መርሐግብር ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 190 ተማሪዎችን አስመርቋል።

‎ኮሌጁ ከመማር ማስተማር ጎን ለጎን ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማከናወን ማህበራዊ ሀላፊነቱን እየተወጣ ሲሆን COC ማዕከል ሆኖም እያገለገለ ይገኛል ተብሏል።

‎የዕለቱ የክብር እንግዳና የአርባምንጭ ግብርና ምርምር ማዕከል ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ቱማ አየለ፤ ተመራቂ ተማሪዎች በተማሩበት ሙያ መስክ ሥራ ጠባቂ ከመሆን ሥራ ፈጣሪ በመሆን የሀገሪቱን ልማት ለማፋጠን የበኩላቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

‎ተመራቂ ተማሪዎች በሰለጠኑት ሙያ ሥራ ጠባቂ ሳይሆን ሥራ ፈጣሪ በመሆን ሀገራቸውን ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

‎በዕለቱ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂ ተማሪዎች የዋንጫና መዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

‎ዘጋቢ፡ አለሚቱ አረጋ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን