“ትንንሽ የሚመስሉ ስራዎች ለትልልቅ ዕድሎች በር ይከፍታሉ” – ወይዘሮ ህልውና ጌታቸው

በአለምሸት ግርማ

የዛሬዋ እቱ መለኛችን ወይዘሮ ህልውና ጌታቸው ትባላለች። ትውልዷና ዕድገቷ የፍቅር ከተማ በሆነችው በድሬዳዋ ነው።

መደበኛ ትምህርቷንም እዚያው ድሬዳዋ ከተማ በሚገኘው አቡነ እንድሪያስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በመግባት እስከ ስምንተኛ የተከታተለች ሲሆን፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷ ደግሞ በድሬዳዋ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመከታተል አጠናቃለች።

በመቀጠልም ባገኘችው የትምህርት ዕድል ወደ ሃዋሳ ቴክኒክና ሙያ በመምጣት በወተር ሰፕላይ ዘርፍ በዲፕሎማ በ1998 ዓ.ም ተመረቀች።

ከዚያም በቤንች ማጂ (ሰሜን ማጂ ወረዳ) በመመደቧ ኑሮዋን እዚያው አደረገች። በዚያም ለሁለት ዓመታት ያህል በሙያዋ አገልግላለች። ስራዋ በአብዛኛው የመስክ እንደነበርም አጫውታናለች።

በዚህ መሐል ነበር የዛሬውን ባለቤቷን የተዋወቀችው። እሱ የሚሰራው ክልል ተቋም ላይ ስለነበር በተለያየ አጋጣሚ በዚያ ለነበሩ ባለሙያዎች ስልጠና ይሰጣቸው ነበር። ትውውቃቸውም አሰልጣኝና ሰልጣኝ በነበሩበት ወቅት ነበር።

በዚያ አጋጣሚ የተጀመረው ፍቅር እያደገ መጥቶ ወደ ትዳር ደረጃ ደረሰ። በዚህም ምክንያት ስራዋን ትታ የትዳር አጋሯ ያለበት ሃዋሳ ከተማ ጓዟን ጠቅልላ መጣች፤ ወዲያውም የመጀመሪያ ልጇን ጸነሰች።  ልጇን በሰላም ከተገላገለች በኋላ ሙሉ ጊዜዋን ሰጥታ በማሳደግ የእናትነትን ኃላፊነት መወጣት ጀመረች።

ልጇ ሁለት ዓመት ከሞላው በኋላ ግን በዚያው መቀጠል አልፈለገችም። ይልቁንም ስራ መስራት እንዳለባት ወሰነች። ልጇን ማዋያ በማስገባት የግለሰብ ኮምፒውተር ቤት በ3 መቶ ብር ተቀጥራ መስራት ጀመረች። አንዳንዶች “እንዴት በዚህ ብር ትሰሪያለሽ ባልሽ ምን አሳጣሽ” እያሉ ቢወተውቷትም ልትሰማቸው ግን አልፈቀደችም።

“ባሌ ምንም አላሳጣኝም፤ ሁሉን አሟልቶ እያኖረኝ ነው፤ ግን ሰው ስለሆንኩ መስራት አለብኝ የሚል ምላሽ ነበር የሰጠኋቸው። በዚያ አቋሜ ፀንቼ ስራዬን ቀጠልኩ። ጥሩ የሆነ የኮምፒውተር ችሎታ ቢኖረኝም፤ አሰሪዬ መልካም ሰው ስለነበር የማላውቃቸውን ነገሮች እንዳውቅ እረድቶኛል።

“በዚህ መሐል የተለያዩ ትምህርት ቤቶች እየመጡ ፈተና ያሰሩን ነበር፡፡ ከነዚህም መካከል አንዱ በሀዋሳ ከተማ የሚገኘውና የግል ትምህርት ቤት የሆነው ማውንት ኦሊቭ ነበር። በዚያም ስራዬን ፍጥነቴን አይተው ስለወደዱት ‘ለምን እኛ ጋር አትሰሪም?’ የሚል ጥያቄ አቀረቡልኝ፡፡ እኔም ክፍያው የተሻለ ስለነበር ተስማምቼ በእናት ማውንት ኦሊቭ በፀሐፊነት መስራት ጀመርኩ።

“በዚያም ወቅት በጠዋት ተነስቼ ልጄን አሰናድቼ ወደ ማዋያ ካደረስኩ በኋላ ወደ ስራዬ እሔዳለሁ፤ እንደገና ከስራ ወጥቼ ልጄን አመጣለሁ። ከቀን ወደ ቀን ትልቅ ጫና ፈጠረብኝ፤ ምንም ትርፍ የሚባል ጊዜ አጣሁ። በዚህ ወቅት ነበር ‘ተቀጥሬ እንዲህ መትጋት ከቻልኩ የራሴን ስራ ለምን አልጀምርም’ የሚል ሃሳብ በአዕምሮዬ የመነጨው።

“በዚህም ለስድስት ወራት ከሰራሁ በኋላ ስራዬን ለቅቄ ወደ ራሴ መዘጋጀት ጀመርኩ፤ ቀድሜም ሃሳቡን ለባለቤቴ አማከርኩት። ነገር ግን በንግድ ዘርፍ ምንም ልምድ ስላልነበረኝ የምከስር መስሎት ብዙም ፈቃደኛ ሊሆን አልቻለም። ከዚያም ሃሳቡን ለቤተሰቦቼ አጋራኋቸውና መነሻ እንዲሰጡኝ ጠየኳቸው።

“በሃሳቤ ተስማምተው አስር ሺህ ብር ሰጡኝ። ያንን ብር ይዤ ለስራ የሚሆን ቦታ እያፈላለኩ እያለ፤ ከዕለታት በአንዱ ቀን ከቤተክርስቲያን ስመለስ አሁን የምሰራበት ቤት ‘ይከራያል’ ተብሎ ማስታወቂያ ተልጥፎበት ነበር። ለሰፈሬም ቅርብ ስለነበር ጊዜ ሳላባክን ቤቱን ተከራየሁት።

“የሶስት ወር ሶስት ሺህ ብር ከፈልኩ። በሰባት መቶ ብር ደግሞ ዲስፕሌይ ገዛሁና ሲመጣ በሩ ጠባብ ስለሆነ አላስገባም አለ። እንደገና ለባለሙያ ሶስት መቶ ብር በመክፈል ተቀንሶ ነበር ወደ ውስጥ የገባው። በቀረው ስድስት ሺህ ብር ነበር ስራዬን የጀመርኩት።

“መነሻዬ ዝቅተኛ መሆኑና ባለቤቴም በደንብ ፍቃደኛ አለመሆኑ፤ በወቅቱ ትልቅ ማነቆ ሆኖብኝ ነበር። ይሁን እንጂ ስራዬን በትጋት ነበር የምሰራው። ለሱቅ የሚሆኑ የንግድ ዕቃዎቼን የማመጣው ከአዳማ ነበር። የምሔደው ደግሞ ደርሶ መልስ ስለነበር አድካሚ ነበር።

“ቶሎ ለመድረስ ሲባል ምግብ ሳይበሉ መሔድ አለ፤ መቸገርም ያጋጥማል። በወቅቱ የሺቲዎች ጥሩ ስፌትም እዚው ነበር የሚሰራው። እና አንዳንዴ ነይ ችግር የለም ይሉና እዛ ስደርስ ወይ ሳያልቅ እደርሳለሁ፤ ወይም ሰዎቹ ላይኖሩ ይችላሉ።

“ከዚህ የተነሳ አንዳንዴ ደብረ ዘይት ቤተሰብ ጋር ነበር የማድረው። ተቀጥሬ በራሴ መኖርን ስለለመድኩ መቀመጥን አልፈለኩም። ችግሮች ቢኖሩም ስራዬን ማቋረጥ ግን አልፈልግም ነበር።

“እንደዛም ሆኜ ያመጣሁትን ሸጬ ተመልሼ እንደገና ደግሞ እሔዳለሁ። ባለቤቴም ድካሜን ሲያይ ያዝንልኝና አንዳንዴ ሔዶ ዕቃ ያመጣልኛል። ከቆይታ በኋላ ከአጠገቤ ያለው ሱቅ ሲለቀቅ ሰፋ ይል ስለነበር ወደዚያ ቀየርኩ። እኔ የለቀኩት ቤት የገባችው መምህርት ነበረች።

“በትርፍ ጊዜዋ ነበር ስፌት የምትሰራው። ከተግባባን በኋላ ለምን አዳማ ትመላለሻለሽ ራስሽ ለምን አትሰሪም የሚል አሳብ አመጣች። እኔም በነገሩ ላይ ማሰብ ጀመርኩ። በግል ለመሰልጠን እያሰብኩ እያለ በአጋጣሚ በሰፈር የልማት ቡድን እሳተፍ ስለነበር በዚያ የስልጠና ዕድሉ መጣ።

“መስፈርቱ ደግሞ ስምንተኛ ክፍልን ያጠናቀቀ የሚል ነበር። በዚህም መሰረት መስፈርቱን የምናሟላ አምስት ለምግብ ዝግጅት፤ አምስት ደግሞ ለልብስ ስፌት ስልጠና ተመለመልን። እኔም ከልብስ ስፌት ሰልጣኞቹ መካከል ነበርኩ። ለሶስት ወራት በኮምቦኒ የሴቶች ሙያ ማሰልጠኛ ማዕከል ከሰለጠንን በኋላ የምስክር ወረቀት ተሰጠን። እንዲሁም ለሁለት አንድ የልብስ ስፌት ማሽን ለስራ ተበረከተልን።

“ማሽኑ ማኑዋል ስለነበር ዲናሞ በማስገጠም በኤሌክትሪክ መስራት ጀመርኩ። አብረን ከሰለጠንነው እስካሁን በሙያው ላይ ያለሁት እኔ ብቻ ነኝ። እና በልብስ ስፌት ስራ በመጀመሪያ ስራዬ 30 ብር ነበር ያገኘሁት። በዚያም በጣም ተደስቼ ነበር። ብሩ ብቻ ሳይሆን ስራውን ለምጄ ያገኘሁት ስለሆነ ብሩ በወቅቱ ለእኔ ትልቅ ዋጋ ነበረው።

“በመቀጠልም አቢሲኒያ ባንክ በመሔድ የቁጠባ ሙዳይ አመጣሁና መቆጠብ ጀመርኩ።  በመጀመሪያ ቁጠባዬም የገዛሁት ስልክ ነበር። በአጋጣሚ በወቅቱ ስልኬ ጠፍቶብኝ ስለነበርና ለስራዬም ስለሚያስፈልገኝ ሳልቸገር ገዛሁ።

“ስራው እየለመደ ሲመጣ ጊዜያዊ አጋዥም ቀጠርኩ። በሒደት ያሉኝ ማሽኖች በቂ እንዳልነበሩ ስረዳ ተጨማሪና የተሻሉ ማሽኖችን ለመግዛት ወሰንኩ። በዚህም መሰረት ዓላማዬን ለማሳካት በመቆጠብ ዘመናዊ የልብስ ማሽን፣ የጥልፍ ማሽን፣ ኦቨርሎክ ማሽን ለመግዛት በቃሁ።

“በመቀጠልም እዚሁ መደዳ ላይ የሀገር ልብስ ቤት ከፍቼ ሰባት ሰራተኞችን ቀጥሬ መስራት ጀመርኩ። ለአንድ ዓመት ያህል ስራው ጥሩ ነበር። ሆኖም ቦታው ገባ ያለ ስለነበር ገበያው ሊቀጥል አልቻለምና ተውኩት። በአሁኑ ወቅት እነዚህ ሁለት የተያያዙ ሱቆች የሀገር ልብስ ስፌት፣ ጥልፍ፣ ሽፎን፣ ሺቲ የመሳሰሉትን እንሰራለን።

“የሴቶች ውበት መጠበቂያዎችም አሉን። ሶስት ቋሚ ሰራተኞች ያሉኝ ሲሆን፤ ሁሉም ሴቶች ናቸው። ምክንያቴ ደግሞ ሴቶች ጠንቃቃና ኃላፊነት የሚሰማቸው ስለሆኑ ነው። በተጨማሪ የበዓላት ስራዎችና ልዩ ትዕዛዝ ሲመጣ በውጭ የማሰራቸውም አሉ።

“አብዛኛውን ስራዬን የምቀበለው በትዕዛዝ ነው፤ ደንበኞቼ የሚፈልጉትን ዲዛይን ሰርቼ አቀርባለሁ። በብዛት ሲመጡ ደግሞ የዋጋ ቅናሽም አደርጋለሁ። ከዚህ በተጨማሪ ሁለት ጊዜ ባዛር ላይ ተሳትፌያለሁ። በዚያም ልምድም ጥቅምም አግኝቼበታለሁ። በቀጣይ ስራዬን የማሳደግ ፍላጎት አለኝ።

“የአሁኑን ባዛር ያልተሳተፍኩት ትኩረቴን ሌላ ቅርንጫፍ ለመክፈት በጀመርኩት ጉዳይ ላይ በማድረጌ ነው። አሁን ካለሁበት የተሻለ እይታ ያለው ቦታ ላይ ለመክፈት በሒደት ላይ ነኝ። እግዚአብሔር ቢፈቅድ ወደፊት ወደ ጋርመንት ለማደግ ነው የምፈልገው” በማለት ነበር አሁን ያለችበትንና የወደፊት ዕቅዷን ያጋራችን።

ዝቅ ብሎ መስራት ወደሚፈልጉት ደረጃ ያደርሳል የምትለው ወይዘሮ ህልውና፤ ሴቶች ስራን ሳይንቁ መስራት አለባቸው ትላለች።

“በስራ ህይወት ውስጥ መውደቅና መነሳት ያጋጥማል። እኔ እዚህ የደረስኩት ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፌ ነው። ስለዚህ የሚፈልጉትን እስኪያገኙ ድረስ መቀመጥ የለባቸውም፤ ትንንሽ የሚመስሉ ስራዎች ከትልልቅ ዕድሎች ጋር ሊያገናኙ ይችላሉ። በተለይ ወጣት ሴቶች ስራን ሳይመርጡና ሳይንቁ መስራት ቢችሉ መልካም ነው። መስራት እየቻሉ የሰው እጅ ማየት ተገቢ አይደለም። በተለይ በአሁኑ ወቅት ለሴቶች ብዙ የስራና የብድር አማራጭ ስላለ ቢጠቀሙበት” በማለት ምክሯን ለግሳለች።