የህግ ታራሚዎችን በስነ ምግባር ለማነፅ በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው የጉራጌ ዞን ፍትህ መምሪያ ገለፀ

መምሪያው ለወልቂጤ ማረሚያ ተቋም ታራሚዎች የመጽሐፍትና የአልባሳት ድጋፍ አድርጎል።

የጉራጌ ዞን ፍትህ መምሪያ ሀላፊ አቶ ኤልያስ ሰብለጋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ተቋማቸው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የማረሚያ ተቋሙ የስራ እንቅስቃሴን በሚመልከት ታራሚዎችን የመጠየቅና የሚስተዋሉ ችግሮችን የመቅረፍ ስራ እየሰራ ይገኛል።

መምሪያው በማረሚያ ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች በተለያዩ ጊዜያት ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቁመው፤ ከተለያዩ አካላት ያሰባሰባቸውን የመጽሐፍትና የአልባሳት ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል አቶ ኤልያስ።

ታራሚዎች በቆይታቸው የተለያዩ እውቀቶችንና ክህሎቶችን አግኝተው ወደ ማህበረሰቡ ሲመለሱ በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፍ አምራችና ሀገር ወዳድ ዜጋ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በተቋሙ የታራሚዎች የሰብአዊ መብት አያያዝ የተሻለ መሆኑን የገለፁት አቶ ኤልያስ፤ የምግብ አቅርቦት፣ የአልባሳት፣ የመኝታና ሌሎችም አገልግሎቶችን የማሻሻል ስራ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በተለይም ከዚህ ቀደም እየተስተዋለ የነበረውን የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ማሻሻል መቻሉን የተናገሩት ሃላፊው፤ በቀጣይም የታራሚዎች የክፍል ጥበትና ሌሎችም ችግሮችን ለመቅረፍ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አብራርተዋል፡፡

በጎነት ለራስ በመሆኑ የታራሚዎች ችግርን በመገንዘብ የተለያዩ ረጂ ተቋማትና ግለሰቦች ለታራሚዎች እያደረጉት ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልፀዋል፡፡

የወልቂጤ ማረሚያ ተቋም ሀላፊ ኮማንደር ታምሬ ደንድር በተቋሙ ከ9 መቶ በላይ የህግ ታራሚዎች የሚገኙ ሲሆን ከማረምና ማነጽ ባሻገር በተቋሙ ቆይታቸው በተለያዩ ስራ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው እንዲሰሩ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

ዞኑ በህግ ጥላ ስር ለሚገኙ ታራሚዎች ስለተደረገው ድጋፍ አመስግነው፤ ሌሎችም በመሠል መልካም ተግባራት ላይ እንዲሳተፋ ጥሪ አቅርበዋል።

የተቋሙ ዋና ዓላማ በወንጀል የተሳተፉ ዜጎችን አርሞና አንጾ ማውጣት ብቻ ሳይሆን እራሳቸውን በእውቀት እንዲያሳድጉ ከወልቂጤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ጋር በጋራ እየሰሩ እንደሆነም ገልጸዋል።

አስተያየታቸውን የሰጡን የህግ ታራሚዎች ከዚህ ቀደም በማረሚያው ቤተ-መፅሀፍ ውስጥ በቂ መጽሐፍ ባለመኖሩ ይቸገሩ እንደነበር አሁን ግን የልዩ ልዩ መጽሐፍትና አልባሳት ድጋፍ በመደረጉ መደሰታቸውን ገልፀዋል፡፡

በማረሚያ ቤቱ በሚኖራቸው ቆይታ በስነ ምግባር በመታነፅና ልዩ ልዩ የሙያ ስራዎችንና ልምዶችን ቀስመው በመውጣት በቀጣይ ማህበረሰባቸውን በተሻለ መልኩ ለማገልገል እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

በባለድርሻ አካላት የሚደረጉ መሰል ድጋፎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ደጋጋ ሂሳቦ – ከወልቂጤ ጣቢያችን